የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ፖሊሲው የአካል ጉዳተኞችን መብቶች እና ጥቅሞች ሙሉ እንዲያስጠብቅ ሆኖ መዘጋጀቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገልጸዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው ተዘጋጅቶ ለፕላን እና ልማት ሚኒስቴር መላኩን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በቅርቡ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ብለዋል።
የብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ፖሊሲ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች ሙሉ ተሳትፎ እና እኩል ዕድል በማረጋገጥ አካታች ኅብረተሰብ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊሲው ህንፃዎችን፣ መጓጓዣዎችን እንዲሁም መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ መሠረት ልማቶችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።
ልዩ ፍላጎት ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሆነ የትምህርት ሥርዓት እንዲስፋፋ ማድረግ፣ የሥራ ስምሪት ዕድሎችን እና የገቢ ምንጮችን ማስፋት እንዲሁም በአሠሪዎች የሚደርስባቸውን መድልዎ ማስቀረትም የፖሊሲው አካል ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፥ ፖሊሲው የሁሉም የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ተወካዮች ተሳትፈውበት በልዩ ሁኔታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው በሚመለከተው አካል በፍጥነት ጸድቆ ወደ ትግበራ እንዲገባም ዋና ዳይሬክተሩ አካል ጉዳተኛችን በመወከል ጠይቀዋል።
በላሉ ኢታላ
#ebcdotstream #ethiopia #feapd #mowsa #specialneeds #differentlyabled