Search

ቀይ ባሕርን በጋራ መጠቀም ከተቻለ የተሻለ ውጤት ይገኛል - የቀድሞ የባሕር ኃይል አባላት

ማክሰኞ ጥቅምት 25, 2018 34

ቀይ ባሕርን በጋራ መጠቀም ከተቻለ በልማትም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ሲሉ የቀድሞ የባሕር ኃይል አባላት ተናገሩ።
የቀድሞ የባሕር ኃይል አባል የሆኑት ማስተር ቺፍ ዘሪሁን ወዬሳ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይን በተመለከተ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እየሄደችበት ያለው መንገድ ተገቢና ፍትሐዊ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ቀይ ባሕርን በጋራ ብንጠቀም ለተሻለ ትብብር በር የሚከፍት ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ቀይ ባሕር ሰፊ ሃብት የያዘ በመሆኑ ለቀጣናው ሀገራት ሁሉ ይበቃል፤ ስለዚህ በጋራ ብንጠቀም ምንም አይነት አሻሚ ጉዳይ አይነሳም ሲሉም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተነሱ ጫናዎችን በመቋቋም ግድቡን ማጠናቀቋን አስታውሰው፤ በቀጣይም የባሕር በር ጥያቄ የማይመለስበት ምክንያት እንደማይኖርም ነው ያነሱት።
የቀድሞ የባሕር ኃይል አባል ሊዲንግሲማን ጥበቡ ተፈራ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ቢኖራት የቀጣናውን ሀገራት ሕዝብ በልማት በማስተሳሰር ረገድ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል ሲሉ ገልጸዋል።
ከባሕር በር ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ አካላት የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ለማሳደር እንደሚፈልጉም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብቷን ሁሉም ዜጋ ሊጠይቅ እንደሚገባው አንስተው፣ ቀደም ባለው ጊዜ በባሕር በር ጉዳይ ላይ የተፈፀመው ስህተት በአዲስ ታሪክ መታደስ እንዳለበትም አመላክተዋል።
 
 
በሜሮን ንብረት