Search

የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማኅበር እና የሳውዲ ዓረቢያው ተቋም ስትራቴጂያዊ ትብብር ፈጠሩ

ዓርብ ጥቅምት 28, 2018 34

የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማኅበር (EYEA) እና የሳውዲ ዓረቢያ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተቋማት ባለስልጣን (ሙንሻአት) በዲጂታል እና በኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች ዘርፍ ትብብርን ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂያዊ ትብብር መፍጠራቸው ተገለጸ።
በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነትም የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብዱልቃድር እና የ"ሙንሻአት" የጋራ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አብዱል ሙህሲን አል ሳሊም ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን በሳውዲ ዓረቢያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) እና የ”ሙንሻአት” ዋና ገዥ የሆኑት አቶ ሳሚ ኢብራሂም አልሁሰይኒ በተገኙበት ተከናውኗል።
ይህ አጋርነት በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ እና በሳውዲ ዓረቢያ መካከል በሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎች እና ስታርት አፖች መካከል ትርጉም ያለው ትብብርን ለማሳደግ ያለመ ነው።
ትብብሩ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን፣ የጋራ ሥራዎችን፣ የአቅም ግንባታን እና ድንበር ተሻጋሪ የገበያ ተደራሽነትን ለማገዝ እንደሚረዳ ተመላክቷል።
በተጨማሪም የወጣቶችን ፈጠራ ለማሳደግ፣ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ አሠራሮችን ለማስተዋወቅ እና ወጣቶች ሁሉን አቀፍ ዕድገትን እንዲያመጡ እንዲሁም የረጅም ጊዜ የልማት ግቦች ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ዘላቂ የሥራ ፈጠራ ሥርዓቶችን ለማጠናከር የሚያስችል ትብብር መሆኑ ተገልጿል።
በመጨረሻም በዚህ ስምምነት "ሙንሻአት" ከሁለቱም ወገን ያሉ ሥራ ፈጣሪዎች ውጤት በማስመዝገብ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንዲጠቀሙ፣ በዓለም ዙሪያ ካሉ የሥራ ፈጣሪ ድርጅቶች ጋር ትብብርን እንዲያስፋፉ እና ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እድገትና ዘላቂነት የሚያበረታታ የተቀናጀ የንግድ ከባቢን እንዲፈጥሩ እንዲሁም ከሳውዲ አረቢያ ራዕይ 2030 ዓላማዎች ጋር እንዲጣጣሙ የሚያስችል - ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ገበያዎችን እንዲያገኙ ለማስቻል የሚሰራ መሆኑ ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ማኅበር የወጣቶችን የመፍጠር አቅም ለማጎልበት የሚሠራ ማኅበር ሲሆን፣ የማኅበሩ ዓላማ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እና ሃብት ማቅረብ እንዲሁም ቢዝነሶቻቸው ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ የፈጠራ ሐሳቦችን የሚያገኙበትን ትስስሮችን መፍጠር ነው።
በስትራቴጂያዊ ምሰሶዎቹ እና ኢኒሼቲቮቹ አማካኝነትም ትብብርን፣ ፈጠራን እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያበረታታ ሕያው ሥነ-ምኅዳር ለመገንባትም ይሠራል።
 
በጌትነት ተስፋማርያም