Search

ተበዳይ ፍትሕን የማያጣበት የጌዴኦ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት - ‘ጋፌ’

እሑድ ጥቅምት 30, 2018 142

‎በጌዴኦዎች የሚተገበር ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ‘ባሌ’ ይባላል። ‎ከዚህ የሚቀዳው የዳኝነት ሥርዓት ደግሞ ‘ጋፌ’ በመባል ይታወቃል።
‘‎ጌርቹማ’ ወይም ‘ፋጬኤ’ በሚሉ ተለዋጭ ስሞችም የሚገለጽ ሲሆን፣ የዳኝነት ሥርዓቱ የሚፈፀምበት ስፍራ ደግሞ ‘ሶንጎ’ የሚል ስያሜ አለው።
ለዚህ ተግባር የተመረጡ ዳኞች ‘ባጤቲ ሃይቻዎች’ እና ‘ሁላቲ ሃይቻዎች’ በተመረጡ ቀናት ለዳኝነት ይሰየማሉ። ‎ሰኞ እና ሐሙስ መደበኛ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቀናት ናቸው።
በባህላዊ የዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ገንዘብ ተበድሮ መካድ፣ በጋራ የሚሠራ ንግድ ውስጥ የሚከሰት አለመግባባት፣ ወሰን መግፋት፣ ትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና የንብረት ክፍፍልን የመሳሰሉ ጉዳዮች ታይተው ውሳኔ ያገኛሉ።
ዛሬም ቢሆን ሰዎች ፍትሕን ፈልገው ለሶንጎው አቤት ይላሉ። ‎ተበዳይ የደረሰበትን በደል ለዳኞች ያብራራል፤ በዳይ ተብሎ የቀረበውም ግለሰብ አለኝ ያለውን እውነት በዳኞች ፊት ያቀርባል።
ክርክሩ በዚሁ መልክ ቀጥሎ በዳይ የተባለው ሰው ድርጊቱን አልፈፀምኩም ብሎ ክዶ ቢከራከር፣ በዳኞች ሁለት ጥያቄ ብቻ ይቀርብለታል "አድርገኻል? ወይስ አላደረግኽም?" የሚል።
‎በዳይ “አላደረግኹም” ካለ ‎ዳኞች ወደ ከሳሽ በመዞር "ያልበደለህን ለምን ከሰስህ?" ይሉታል።
 
ተበዳይ ከተፈጥሮ የሚቀዳውን፣ የሚመለከተውን ዐይን፣ ጆሮ እና አንደበቱን ምስክር አድርጎ ያቀርባል።
በዳይ ከዚህ በኋላ ማምለጫ የለውም። የወሰደውን ይመልሳል፤ ተበዳይን ይክሳል።
በዚሁ በ‘ጋፌ’ የዳኝነት ሥርዓት በተጠናቀቀው የጥቅምት ወር ብቻ 17.9 ሚሊዮን ብር ከበዳዮች ለተበዳዮች ተመላሽ መደረጉን የጌዴኦ ዞን ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ደርቤ ጅኖ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ተናግረዋል።
በ2017 ዓ.ም. በባህላዊ ‘ሶንጎዎች’ በገንዘብ 20 ሚሊዮን ብር ለባለቤቶቻቸው እንዲመለስ ማስቻላቸውንም ኃላፊው ጠቁመዋል።
‎እንደ አቶ ደርቤ ገለጻ፣ ‘ሶንጎዎቹ’ በዞኑ ባሉ ወረዳዎች በሚሰጡት የዳኝነት አገልግሎት የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ሸክም አቅልለዋል፤ የጊዜ ብክነትንም አስቀርተዋል።
በሲሳይ ደበበ