Search

በሀገር ግንባታ ሒደት ወሳኝ ድርሻ ያለው የምክክር መድረክ

እሑድ ጥቅምት 30, 2018 144

ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ መሠረት የሚጥል እና ለአሁኑም ሆነ ለቀጣይ ትውልድ የሚበጅ መፍትሔ የሚገኝበት ነው ሲሉ ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ገለጹ።
በኢትዮጵያ ተከስተው ለነበሩ የተለያዩ ችግሮች ኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል ትልቅ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ምሁራኑ፣ በዚህ ረገድ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እና ኅብረ ብሔራዊነትን ለማጠናከር ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ሳይንስ እና የዲፕሎማሲ መምህር የሆኑት እንዳለ ንጉሴ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ነገሮችን በሰላም ከመፍታት ይልቅ ወደ ፀብና አለመግባባት እንዲያመራ የሚያደርግ ነበር ብለዋል።
በሀገራዊ የምክክር መድረክ ችግሮችን እያነሱ በመወያየት የጋራ ጉዳዮች ላይ መግባባትን መፍጠር የሚቻልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን አመላክተዋል።
ሀገራዊ የምክክር መድረክ ለሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ዜጋ በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማካሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አድማሱ ገበየሁ (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ ሀገራዊ የምክክር መድረክ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ ዕድሉን መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ሀገራዊ ምክክር ለአሁኑ ትውልድ እና ለቀጣይ ትውልዶች የሚበጅ መፍትሄ የሚገኝበት መድረክ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ይዞት የሚመጣውን መፍትሄ ተስፋ በማድረግ ለስኬታማነቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲሉም አመላክተዋል።
ከእኔነት ይልቅ እኛነትን ያስቀደመ፣ ከመንደር ወደ ሀገር ያደገ የፖለቲካ ተሳትፎ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፣ ከዚህ የተለየ ተግባር ግን መሠረታዊ የፖለቲካ ምንነትን የዘነጋ ተግባር በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
 
 
በሃይማኖት ከበደ