ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና የሥራ ቅጥሮች በሕጋዊ እና መንግሥት ባስቀመጠው አሠራር ብቻ ሊሆን እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስገነዘበ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቋል።
ከውጭ ግንኙነት ቁልፍ ሥራዎች አንዱ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ በፖሊሲው አማካኝነት በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን መብት የማስከበር፣ ለዜጎች ተገቢ የቆንስላ አገልግሎት የመስጠት፣ በሄዱበት ሀገር ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው እና የሀገሩ መንግሥት ዜጎቻችን ሀገራቸውን እንዲለቅቁ ሲወስን መብታቸው፣ ክብራቸው እና ደኅንታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የመካከለኛ ምሥራቅ፣ የአፍሪካ እና እንደ ማይናማር ያሉ የእስያ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁሟል።
ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ በሳዑዲ ዓረቢያ በተለያዩ እስር ቤቶች እና ማቆያ ማዕከላት የሚገኙ ከ17 ሺህ በላይ ዜጎቻችን መመለስ መቻሉን እና በአሁኑ ወቅትም በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የመመለሱ ሥራ መቀጠሉን በመግለጫቸው ላይ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ በየመን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 36 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን ሌሎችንም አስፈላጊውን የሰነድ ማጣራት በማድረግ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ጋር በመቀናጀት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
በማይናማር፣ ላኦስ እና ካምቦዲያ እንዲሁም በሌሎች ሀገራት በተመሳሳይ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎቻችን የመመለስ ጥረት መቀጠሉንም አስታውቋል።
ሆኖም ግን አሁንም ድረስ ዜጎች በተሳሳተ መረጃ በሕገ-ወጥ ደላሎች ተታለው ወደ ተለያዩ ሀገራት በመጓዝ ለእስራት እና ለሞት እየተዳረጉ በመሆኑ ዜጎች ከሕገ-ወጥ ጉዞ ራሳቸውን እንዲከላከሉ እና እንዲጠነቀቁ ሚኒስቴሩ በመግለጫው አሳስቧል።
ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረጉ ጉዞዎችና የሥራ ቅጥሮች በሕጋዊና መንግሥት ባስቀመጠው አሠራር ብቻ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝቧል።