Search

"ከካንሰር ህክምና ጎን ለጎን መጽሐፌን እየጻፍኩ ነው" - ወ/ሮ ሌሊሴ ዱጋ

ማክሰኞ ኅዳር 02, 2018 145

ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ በካንሰር ህመም ምክንያት ህክምና ላይ መሆናቸውን  በሚያሳይ መልኩ  በለቀቁት ምስል እና መልዕክት መነጋገሪያ የነበሩት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ  ሌሊሴ ዱጋ "ከካንሰር ህክምና ጎን ለጎን መጽሐፌን እየጻፍኩ" ነው ሲሉ ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 መሰንበቻ መሰናዶ ላይ  በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ  ሌሊሴ ዱጋ  ባጋጠማቸው የካንሰር በሽታ ጆርዳን ሀገር በህክምና ላይ አንደሚገኙም  ገልጸዋል፡፡

ህመሙ የጀመረኝ ቀለል ያለ ጨጓራ በመምሰል ነበር ያሉት ወ/ሮ ሌሊሴ፤ በተደረጉ ምርመራዎች ግን በሽታው ካንሰር ሆኖ መገኘቱን ተናግረዋል።

በህክምና ወቅት ያጋሩት ምስል የዕለት ተዕለት ሁኔታቸውን ለማሳወቅ እና ከበሽተው ጋር ለሚኖሩ ሰዎች እጅ መስጠት እንደማይገባ መልእክት ለማስተላለፍ ያለመ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ፈጣሪን ማወቄ ብርታትን ሰጥቶኛል ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ለረጅም ዓመት በኤች አይቪ ኤድስ ህመም ላይ በመስራታቸው የካንሰርን በሽታ ለመረዳት እንዳልከበዳቸው ነው የተናገሩት፡፡

በቤተሰቦቻቸው እና በወዳጆቻቸው የሚደረግላቸው ድጋፍ ላቅ ያለ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ በህክምና ላይ የሚገኙት ወ/ሮ ሌሊሴ፤ ከህክምናው ጎን ለጎን መጽሐፍትን በማንበብ፣ የስራ ሁኔታቸውን በመከታተል እንዲሁም አመራርነትን በሚመለከት የራሳቸውን መጽሐፍ እየጻፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 

ቱሪዝም ሲነሳ አብረው የሚነሱት ወ/ሮ ሌሊሴ፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ከሀሳብ ተሻግሮ መሬት ላይ በተግባር እየተሰራበት እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡

በዘርፉ እየተከናወነ ባለው ስራ የቱሪዝም ሀብቶች ለሀገሪቱ  የገቢ ምንጭ እየሆኑ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ወ/ሮ ሌሊሴ በቀጣይ በካንሰር በሽታ የሚጠቁ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል የካንሰር ፋውንዴሽን ማቋቋም እንደሚፈልጉም ከመሰንበቻ መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ሌሊሴ ዱጋ በስራቸው ታታሪ፣ ብርቱ እንዲሁም በኦሮሚያ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ላቅ ያለ አበርክቶ እንደነበራቸው ወዳጆቻቸው እና የስራ ባልደረቦቻቸው ይመሰክሩላቸዋል፡፡

ኮሚሽነሯ በተለይም በኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣቸው እና እንደ ቪዚት ኦሮሚያ ያሉ ኢኒሼቲቮችን በማስጀመር በክልሉ የቱሪዝም እድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዳኖሩ ይነገርላቸዋል፡፡ 

በሜሮን ንብረት

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #visitOromia #LandOfOrigins