Search

ፕሮፌሰር ላጵሶ ከከፋፋይ ነጠላ ትርክት ይልቅ በአሰባሳቢ የወል ትርክት ላይ ያተኮሩ የምርምር ውጤቶችን ትተውልን አልፈዋል

ማክሰኞ ኅዳር 02, 2018 140

ለነጠላ ትርክት እውቅና በመንፈግ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ አካታች አድርጎ በማቅረብ ረገድ ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ በብዙ ደክመዋል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ ገለጹ።

የታሪክ ምሁርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጵሶ ጌ. ድሌቦ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ በቀድሞው የታሪክ ፕሮፌሰር የሽኝት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ፕሮፌሰር ላጵሶ ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ብሩህ አዕምሮ ላይ የራሳቸውን ብርቱ ትጋት በማከል ከከፋፋይ ነጠላ ትርክት ይልቅ በአሰባሳቢ የወል ትርክት ላይ ያተኮሩ የምርምር ውጤቶችን ትተውልን አልፈዋል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፥ ፕሮፌሰር ላጵሶ ሰው ሆነው፣ ሰውነትን አክብረው፤ በምስጉን ምግባራቸው ግብረ ገብነትን አስተምረው፤ በሊቅነታቸው ሚዛንን ጠብቀው፤ እውቀት ከእንጀራ የተሻገረ፣ ለሕሊና ያደረ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች የተረፈ እውነት መሆኑን አሳይተው አልፈዋል።

የፕሮፌሰር ላጵሶ ምሁራዊ መንገድ የአጋጣሚ ሳይሆን ከማለዳ ዕድሜያቸው ጀምሮ በየዕድሜ እርከናቸው ከታዘቡት ነባራዊ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተጨባጭ የተቀዳ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ የተነበበው የሕይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፥ ፕሮፌሰር ላጵሶ የኢትዮጵያን መሠረታዊ የታሪክ ፖለቲካ ተረኮች በጥልቅ ምሁራዊ እይታ ሞግተዋል፤ ለዘመናዊ የመንግሥት አፈጣጠር አማራጭ ትርጓሜዎችን አቅርበዋል፤ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር ጥንስስ ምሁራዊ ንድፍ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በተሟላ አስተውሎታቸው፥ ሀቃቸው ለተደበቀ ባለታሪኮች ብቻ ሳይሆን በተዛባ የታሪክ ገጽ ለተከተቡ ሁሉ እውነት ፀሐይ ሆኖ እንዲወጣላቸው ደክመዋል፤ በዚህም በደንብ የሚያውቋቸው፣ በጥልቀት የተረዷቸው፣ በሚናዛናዊነት የሚያዩዋቸው፣ ፕሮፌሰር ላጵሶን ከታሪክ ምሁር በላይ እንደነበሩ ይመሰክሩላቸዋል።

በመሐመድ ፊጣሞ