ተወዳጁ ድምጻዊ ዳዊት መለሰ ከ23 ዓመታት በኋላ 'ምስጢር' የተሰኘውን የአልበም ስራውን በዛሬው ዕለት በዲጂታል መንገድ ለአድማጮቹ እንደሚያደርስ አሳውቋል።
ድምጻዊ ዳዊት መለሰ በ1959 ዓ.ም በአዲስ አበባ ነው የተወለደው። በፈለገ ዮርዳኖስ፣ በጥቁር አንበሳ እና ቦሌ የተማረው ዳዊት፤ ከሮሃ ባንድ ጋር በፕሮፌሽናል የሙዚቃ ባለሙያነት ነው ዋናውን የሙዚቃ ሕይወት የጀመረው።
በ1976 ዓ.ም በደርግ ዘመን በኪነት በአማተርነት ደረጃ ወደ ሙዚቃው ዓለም ሲቀላቀል ከእንግሊዘኛ ዘፋኝነት በተጨማሪ ድራም ይጫወት ነበር። በተለይም የማይክል ጃክሰን ዘፈኖችን አድናቂና የዘፈን ሕይወቱ ማሟሻ ሥራም የእርሱ ነበር።
በዘፋኝነት ሙያ ውስጥ (ፕሮፌሽናል) ሆኖ መሥራት እንደሚፈልግ ለአባቱ ሲነግር 'ዘፋኝነቱ ላይ በርታበት ነገር ግን ትምህርትህን አትርሳ' ብለውት እንደነበር ያስታውሳል።
በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በተጋባዥነት ይጫወት የነበረው ዳዊት በሮሃ ባንድ ውስጥ ከመሐሙድ አህመድ፣ ከኩኩ ሰብስቤ፣ ከነዋይ ደበበ እና ከተክሌ ተስፋዝጊ ጋር ሆኖ በእንግሊዘኛ ብቻ ይጫወት ነበር።
ከአማርኛ ዘፈኖች ውስጥ 'ሴት አላምንም' እና 'ገዳም' ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ የተጫወታቸው ዘፈኖቹ ናቸው።
በ1983 የመጀመሪያ አልበሙ የሆነው 'አልቻልኩም'ን ሙሉ በሙሉ በአበበ መለሰ ግጥምና ዜማ ደራሲነት፤ በሮሃ ባንድ አጃቢነት ለአድማጭ አድርሷል። በጊዜው በሀገሪቱ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ አልበሙ እምብዛም የመደመጥ ዕድል ባያገኝም ለየት ያለ የአዘፋፈን ስልቱ ግን ሙዚቃ ወዳጆች ልብ ውስጥ አስቀምጦታል።
በዚህ አልበም የተካተቱት 'ይበራል ልቤ'፣ 'ነጋ ነጋ' እና 'አልቻልኩም' የተሰኙት ሥራዎች አድማጩን በፍቅር የጣሉ ነበሩ። ዳዊት ከባህላዊ የአዘፋፈን ስልት የራቁና በጊዜው አፈንጋጭ የመሰሉ አዳዲስ ጣዕም ያላቸው ስራዎችን ይዞ መቀላቀሉም የዘመናዊ ሙዚቃ የሽግግር ዘመን ምሳሌ ተደርገው ከሚጠቀሱ ጥቂት ድምጻውያን አንዱ አድርጎታል።
በዘመኑ የግርማ በየነን 'ሴት አላምንም'ን ዘፈን አስፈቅዶ የተጫወተ ምናልባትም የመጀመሪያው ድምጻዊም ሳይሆን እንደማይቀር የነገርለታል፡፡
'ፍቅር በሎተሪ' የተሰኘው ሁለተኛ አልበሙን የያዘ ካሴት በ1987 ዓ.ም ሲያወጣ ተቀባይነት ማግኘት ብቻም ሳይሆን የመጀመሪያ አልበሙም ቀስ በቀስ እንዲደመጥ ምክንያት ሆነ።
ከተመስገን ተካ ጋር ‘ፍቅር በሎተሪ‘ እና ‘አትመኪበት‘ን ጨምሮ ዝነኛ ሥራዎችን አብረው ሰርተዋል። በተለይም ‘ፍቅር በሎተሪ‘ ዓመት የፈጀ ስራው ነበር። ሁለተኛው አልበም አገር ቤት ቢቀረጽም ጥራቱ ጥሩ ስላልሆነ አሜሪካ ለእረፍት በሄደበት ወቅት ነው ዳግም ተቀርጾ የተሰራው። በወቅቱ አበጋዝ፣ ሄኖክ እና ፋሲል ጥሩ ቅጂ ሆኖ እንዲቀረፅ አድርገውለታል። በሲዲ እና በካሴት የታተመ ሥራው ሲሆን፤ የካሴቱ አልበም 10 ሥራ ሲኖረው ሲዲው ላይ 11 ዘፈኖች አሉት። ከአሥራ አንዱ ሥራዎች አንዱም 'Sally' የተሰኘ የእንግሊዝኛ ዘፈን ነው።
በ1992 'አንቺን ነው' ብሎ በሶስተኛ አልበም ወደአድማጭ የተመለሰው ድምጻዊው፤ በተለይ 'አይሰማሽም' እጅግ ከፍ ያለ ተቀባይነት ያገኘበት ስራው ሆኖ አልፏል። በተለያየ ጊዜ ከሌሎች ድምጻውያን ጋር በጋራ ባወጣቸው የአልበም ስራዎች ውስጥም የተወደዱ ስራዎቹን ለአድናቂዎቹ አድርሷል።
'አንድ ቀን' የተሰኘውን አራተኛውና የመጨረሻ የአልበም ስራው በ1995 ዓ.ም ለአድማጮች ያደረሰው ድምጻዊ ዳዊት፤ የአልበሙ መጠሪያ በሆነው ዘፈን 'አይቀርም አንድ ቀን' እንዳለው በመጨረሻ ከረጅም ጊዜ ጥበቃና ናፍቆት በኋላ በሙሉ የአልበም ስራ ሊደመጥ ለዓርብ ህዳር 5 አመሻሽ ቀን ቆርጧል።
የዳዊት መለሰ አዲሱ 'ምስጢር' የተሰኘውና በራሱ የዩትዩብ ገጽ የሚለቀቀው፤ 11 የሙዚቃ ስራዎችን የያዘው አምስተኛ የአልበም ስራው፤ የዘፈን ስብስብ ብቻ ሳይሆን 20 ዓመታትን የፈጀ 'ታሪክ' እንደሆነ ጠቅሷል።
አክሱማዊት ገብረሕይወት