Search

በዓሉ አሰባሳቢ ሀገራዊ ትርክትን ለመገንባት ትልቅ ግብዓት የሚፈጥር ነው፡- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ዓርብ ኅዳር 05, 2018 110

20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አሰባሳቢ ሀገራዊ ትርክትን ለመገንባት እና ለሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ግብዓት የሚፈጥር ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ተናገሩ።
በዓሉ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መሰረት አድርጎ እንዲከበር የክልሉ መንግሥትና ህዝብ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት መግለጫ አመላክተዋል።
አክለውም የህዝቡን አንድነት በማጠናከር የመቻቻል እና የመከባበር እሴቶች እንዲጎለብቱ በዓሉ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ባጠናቀቀችበት እና በጀመረችበት ወቅት ክልሉ በዓሉን ማስተናገዱ ትልቅ ደስታ የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በዓሉ በዋናነት በሆሳዕና ከተማ የሚከበር ቢሆንም፣ በክልሉ ባሉ ሁሉም አካባቢዎች በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በበዓሉ ሲምፖዚየሞች፣ ባዛሮች፣ የውይይት መድረኮች እና የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ጠቁመው፤ ክልሉ በዓሉን እንዲያዘጋጅ እድል በማግኘቱ አመስግነዋል።
በሃይማኖት ከበደ