Search

ትውልድ እና ተቋምን እየገነባን በተለወጠ የሥራ ባህል 24/7 በትጋት እና በቁርጠኝነት እንሠራለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓርብ ኅዳር 05, 2018 139

ትውልድ እና ተቋምን በመገንባት በተለወጠ የሥራ ባህል 24/7 በትጋት እና በቁርጠኝነት እንደሚሠራ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።
“በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ” በሚል መሪ ሐሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በተሰጠው ሥልጠና ላይ በፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ከከተማዋ አመራሮች ጋር መወያየታቸውን ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ጠቁመዋል።
ውይይቱ ዋና ዋና ግቦቹን ወደ ዕቅድ በመቀየር በላቀ አፈፃፀም እና ውጤታማነት መተግበር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ መሆኑንም ገልጸዋል።
አክለውም፣ "እንደ ከተማ የተያዙ ግቦችን ለማሳካት በጠንካራ የአመራር ቁርጠኝነት፣ በፈጠራ እና ፍጥነት መርሕ ግቦቹን ለማሳካት የተዘጋጀውን ዝርዝር ዕቅድ የጋራ አድርገናል" ብለዋል።
ከተለዩት ዋና ዋና ግቦች መካከል የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባን (የፋይዳ ምዝገባ)፤ የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ሥልጣና፤ የተጀመሩ የኮሪደር ልማትን ማጠናቀቅ፣ የወንዝ ዳር ልማት እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን መፈጸም እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል።
ለምርጫ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ግቦችን መቶ በመቶ ማሳካትም በቀጣይ በትኩረት የሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸውን ነው ከንቲባ አዳነች የገለጹት።
የቱሪስት ስበትን፣ የሌማት ትርፋት እና የኢንዱስሪ ምርቶችን መጨመር፤ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፤ ሌብነት፣ ጉቦኝነትን እና ብልሹ አሠራርን ማስወገድም በትኩረት የሚሠሩ ናቸው ብለዋል።
መንደርተኝነትን፣ በአካባቢዊነት ማሰብና መሥራትን እንዲሁም ጠባቂነትን መቀነስ የከተማ አስተዳደሩ አበክሮ የሚሠራበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
"ተረጂነትን እና ልመናን መቀነስ፣ ለልማት መዋል የሚገባውን መሬት ለይቶ ማስቀመጥ፣ ኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ እንዲሁም ሰላማዊ ሁኔታን የሚያውኩ የጥፋት እንቅስቃሴዎችን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት የዋና ዋና ግቦች የትኩረት ማዕከል ሆነው የሚፈፀሙ ይሆናል" ብለዋል ከንቲባ አዳነች።