ክልሉን የቱሪዝም እና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ገለፁ።
አፈ-ጉባኤዋ በሰጡት መግለጫ፤ ክልሉ በይፋ ከተመሠረተ ጥቂት ጊዜ ቢሆንም፣ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ የቱሪስት መስህቦች በማልማትና በማስተዋወቅ ክልሉን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በክልሉ የ165 ኪ.ሜ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎች በመከናወናቸው በርካታ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።
ከተሞችን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ፣ የከተማ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና እና የገጠር ኮሪደር ሥራዎች መሠራታቸውንም አብራርተዋል።
ግብርናን በአዳዲስ እሳቤዎች በመምራትም ያልተለመዱ ምርቶችን በማዘጋጀት ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንደተቻለ አንስተዋል።
በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ብዛት እና የማምረት አቅም በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየታዩ መሆኑን ገልፀዋል።
"ሕብረ ብሔራዊነት እና አንድነትን የሚያጠናክረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክብረ በዓል በክልሉ ያሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል" ያሉት ወ/ሮ ፋጤ፣ በዓሉ የሕዝቦችን ትስስር በሚያጠናክሩ መርሐ ግብሮች እንደሚከበር አስታውቀዋል።
በሀይማኖት ከበደ