Search

የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ውበቷን የገለጠላት ወራቤ ከተማ

ሰኞ ኅዳር 08, 2018 96

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ የቱሪስት መስህብ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ ዞኖችም እነዚህ የልማት ሥራዎች ለነዋሪዎች ምቹ ከተማን በመፍጠር ረገድ ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ነው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በስልጤ ዞን የወራቤ ከተማ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችን በጎበኙበት ወቅት በተለይ ለኢቢሲ ዶት ስትሪም እንደገለጹት፤ የልማት ሥራዎቹ የከተሞችን የኢኮኖሚና የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከማሳደግ አኳያ ከፍ ያለ አስተዋፅዖ አላቸው፡፡
የወራቤ ከተማን አቋርጦ የሚፈሰውን ወንዝ ተገን በማድረግ የተሰራው የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን ውበት ይበልጥ መግለጥ አስችሏል ብለዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታም ብዙ ጥቅም ሳይሰጥ የቆየን አካባቢ በማልማት ለላቀ አገልግሎት መቀየር እንደሚቻል ያሳየ ሥፍራ ነው ሲሉ አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ መንደሩ የሚያስፈልጉት ግብዓቶች የተሟሉለት በመሆኑ፣ ለየትኛውም ኢንቨስትመንት አመቺ በሆነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።
መንግሥት ካስቀመጣቸው አምስቱ ዘርፎች አንዱ ኢንዱስትሪ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋሁን፣ ይህ የኢንዱስትሪ መንደርም ዘርፉን ከማነቃቃት አንፃር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ በበኩላቸው በዞኑ የኢንዱስትሪና የቱሪዝም ዘርፎችን ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በአካባቢው ያሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶችን በማልማት ዘርፎቹ እንዲነቃቁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዞኑ ባለው የመሰረተ ልማት አማራጮችና ለማዕከላዊ ገበያ ምቹ በመሆኑ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርገው የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፤ ይህንን መሰረት በማድረግ በወራቤ ከተማ አንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የቦታ ዝግጅት በማድረግ ኢንቨስተሮችን የመሳብ ሥራዎች መሠራታቸውንም አስታውቀዋል።
ከሁለት መቶ በላይ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪው መንደር መግባታቸውን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ ለግብርና ማቀነባበሪያዎች እና የግብዓት አቅርቦትን ለማሳደግ የሚረዱ ምቹ እድሎች መፈጠራቸውንም ገልፀዋል።
የወራቤ ከተማን ከዚህ በላይ ምቹ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸው፤ 8.4 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያና የህፃናት መጫወቻ ሥፍራዎች ተገንብተው ሲጠናቀቁ የከተማዋን ውበት በይበልጥ የሚገልጡ እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።
በሀይማኖት ከበደ