Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 11 ተጨማሪ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን አዘዘ

ሰኞ ኅዳር 08, 2018 205

የአፍሪካ ግዙፍ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ 11 ተጨማሪ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ውል መግባቱን አስታወቀ።

በዱባይ የአየር ትርኢት ስነ ስርዓት ላይ የተፈረመው የ11 B737-8 ግዢ ስምምነት አየር መንገዱ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን እንዲያሳድግ እና የአዲስ አበባ ማዕከሉንም ለማስፋት እንደሚያስችለው ተጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው "ከዱባይ አየር ትርኢት ጎን ለጎን ተጨማሪ አሥራ አንድ B737-8 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ ጋር ስምምነት ላይ በመድረሳችን ደስተኞች ነን" ብለዋል።

ግዢው አየር መንገዱ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና የደንበኞቹን ምቾት ለመጨመር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፈው የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አየር መንገዱ ባለፉት ዓመታት ከቦይንግ ጋር የነበረውን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

የቦይንግ ሽያጭ እና ግብይት ምክትል ፕሬዚዳንት ብራድ ማክሙለን በበኩላቸው፤ ምቹ እና ዘመናዊ የሆኑት 737 ማክስ አውሮፕላኖች አየር መንገዱ በአፍሪከ፣ መካከለኛ ምሥራቅ፣ ህንድ እና ደቡብ አውሮፓ ለሚገኙት ደንበኞቹ የሚሰጠውን ምቹ፣ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚዱት ተናግረዋል። 

አክለውም "የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀልጣፋ እና ምቹ አውሮፕላኖቻችን ተጠቅሞ የአፍሪካ አህጉርን ከቀረው ዓለም ጋር እያገናኘ በመሆኑ ኩራት ይሰማናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚው የቦይንግ አውሮፕላኖች ተጠቃሚ ሲሆን በርካታ 737 ማክስ፣ 777X እና 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ባለቤት መሆኑን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።  

በለሚ ታደሰ

#EBC #EBCdotstream #EthiopianAirlines #FlyEthiopian #Boeing737Max