አዲሱ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና መሥሪያ ቤት የተደራጀው ሁለመናው የሐሰብ ምንጭ እንዲሆን ተደርጎ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ተናገሩ።
ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ 5 ዓመታት ብቻ ቢሆኑትም፣ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱንም ነው ዶ/ር ወርቁ የተናገሩት።
አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት የተደራጀው የሰው ሠራሽ አስተውሎት እሳቤን መሠረት በማድረግ ‘ስማርት’ ሆኖ ነው ብለዋል።
ይህ የተደረገው ለቢሮ ውበት ብቻ ሳይሆን ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች እያንዳንዱን ውስጣዊ እና ውጫዊ አደረጃጀት ተመልክተው ሀሳብ ማመንጨት እንዲችሉ በማሰብ ነው ብለዋል።
ተቋሙ ባለፉት 5 ዓመታት በየክረምቱ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ተቀብሎ ሲያሠለጥን እንደነበር አንስተው፤ በዘርፉ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቁ ተመራማሪዎች ተቋሙን እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሁሉም ዘርፎች እንደሚያስፈልግ እና በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት ዘርፉን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዓለም በቀጣይ ከነዳጅም በላቀ የሚፈልገው ሀብት ዳታ በመሆኑ፣ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች ዳታቸውን በትክክል መዝግበው እንዲያስቀምጡ ተቋሙ እያገዘ እና ግንዛቤም እየፈጠረ እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ኢንስቲትዩቱ በ5 የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ላይ እየሠራው ያለው የምርምር ሥራ ድምጽን ወደ ጽሑፍ በመቀየር ረገድ የፍርድ ቤቶችን ሥራ እያቀለለ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህ ወደ ሌሎች ቋንቋዎችም እንደሚሰፋ ጠቁመዋል።
ሀገርን ወደፊት የሚወስደው ‘ስታርታፕ’ም ኢንስቲትዩቱ በትኩረት እየሠራበት ያለ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ 5 ወለል ያለው ሕንጻ ለዚሁ ተዘጋጅቶ 200 ስታርታፖች ሀሳቦቻቸውን እያዳበሩበት መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ሀሳብ መንጭቶ እና ዳብሮ ሀገርን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ የነገ ኩባንያዎች የሚፈጠሩበት እንደሚሆን ነው ዶ/ር ወርቁ የተናገሩት።
#EBC #EBCdotstream #AI #startup #DigitalEthiopia