በ9 ክልሎች የሚተገበረው እና 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶአደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ሁለተኛው ምዕራፍ የግብርና ገበያ ተኮር መርሐ ግብር ይፋ ተደረገ።
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና በግብርና ሚኒስትር ለቀጣይ 5 ዓመታት የሚተገበረው የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን የተሰኘው መርሐ ግብር፣ 300 ሺህ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና ስደተኞችን ተደራሽ እንደሚያደርግም ተመላክቷል።
በመርሐ ግብሩ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አካታችና የእሴት ሰንሰለቶችን ማጠናከር ትኩረት እንደሚሰጠው የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ተናግረዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ አነስተኛ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ፣ ሴቶችን እና ወጣቶችን በማብቃት ዘላቂ የእሴት ሰንሰለቶችን በማስፋፋት የግብርናውን አቅም ለምግብ ዋስትና እና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚረዳም ጠቅሰዋል።
የከጉታ ገጠም የሚጠቀሙ አርሶ አደሮችም ወደ የግብርና ቢዝነስ ድርጅቶች እንዲያድጉ በመርሐ ግብሩ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከል መሆኑም ተጠቁሟል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ በ6 ዓመት ትግበራ በ7 ክልሎች 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን አርሶአደሮችን ተደራሽ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ውስጥም 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶአደሮች በኩታ ገጠም የግብርና ሥራቸውን ማከናወን መቻላቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ 2ኛው ምዕራፍ ከመጀመሪያው የቀጠለና የግብርና ምርቶችን በመጨመር ወደ ተጨማሪ ቦታዎች በማስፋፋትና የግል ተሳትፎን በማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በሙሉ ግርማይ