Search

ከመዘግየት ወደ ተስተካካይነት

ማክሰኞ ኅዳር 09, 2018 185

ራሱን እንደቀየረ ንስር አሞራ ሆኖ ብቅ ያለው አዲሱ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ቢሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል።

ይህም በተቋም ግንባታ የግድ አዳዲስ ሕንፃ ገንብቶ ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ባሉት ላይ መሥራት ከተቻለ የተሻለ ውጤት ማሳየት እንደሚቻል አመላካች ነው።

ተቋሙ ያረጀውን ሕንፃ በዘመናዊ መልክ በቴክኖሎጂ በሚመራ መንገድ ካደሰ በኋላ ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ዘርፍ የደረሰችበትን አስገራሚ ምዕራፍ የሚያበስሩ ምርምሮችን አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምረቃው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢንስቲትዩቱ በ5 ዓመታት ውስጥ እዚህ ደረጃ ደረሰ ብሎ መገመት እንደሚከብድ ገልጸው፣ ተቋሙ በአፍሪካም ጭምር በግንባር ቀደምትነት የሚታይ ነው ብለዋል።

በዓለም ዙሪያ በርካታ የኤአይ ተቋማትን የመጎብኘት ዕድል እንደገጠማቸውና የኢትዮጵያው ኢንስቲትዩት ደረጃ ፈጽሞ የማይናቅ መሆኑን ጠቁመውም እጅግ ከፍተኛ አቅም እንደያዘ አስረድተዋል።

የኤአይ ፍሬዎች

የኢንስቲትዩቱ የፈጠራ ሥራዎች ከሮቦት አካላት ማምረትም በላይ የሆነ የሮቦት ሶፍትዌሮችን ጭምር የሚያካትቱ ናቸው። ይህ ይበል የሚያሰኝ ምርምር ድሮኖችን ከማምረት ባሻገር፣ የማነጋገር እና የተሻለ ሥራ እንዲሠሩ የማድረግ አቅምን ፈጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከ100 በላይ አገልግሎቶች የሚሰጠውን የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ሥርዓት የተሠራው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ስኬት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ሊያስወጣ ይችል የነበረውን ወጪ አስቀርቷል። በፋይናንስ ዘርፍም በሀገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ሚሊዮኖች ወጥቶበት የተገዛው "ኢፍሚስ" የተሰኘው ሲስተም በሀገር ውስጥ እየተተካ መሆኑ የሀገር ልጅ አቅምን ያመለክታል።

በጤናው ዘርፍም የጡት ካንሰርን መለየት የሚያስችል ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ሥራ ተሠርቷል።

በግብርናው መስክም በሰብል በሽታ ልየታ፣ በሎጂስቲክስ ቁጥጥር ላይ ኢንስቲትዩቱ የምርምር ውጤቱን አውጥቷል።

ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ዘርፎች አጋዥ ውጤቶችን እያሳየ ቢሆንም፣ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሪ ሐሳቡ "AI for All" ወይም "ኤአይ ለሁሉም ማገዝ እና መጥቀም እንዲችል ማድረግ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የክላውድ ኮምፒውቲንግ እና ቋንቋዎች ቅንብር

ኢንስቲትዩቱ የክላውድ ኮምፒውቲንግ እና ግዙፍ ዳታ ላይ በስፋት እየሠራ ነው። ትልቅ አቅም ያለው ዳታ ማዕከል መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ መረጃውን መሰብሰብ፣ ማቀናበር እና መረጃዎችን ለተጨማሪ ጥቅም እንዲውሉ የማድረግ አቅም በኢንስቲትዩቱ ተፈጥሯል።

ከዳታ አጠቃቀም ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሆኑትን አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎችን በሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂ ምርምር በማበልፀግ ሰዎች ከሌላው ጎረቤታቸው ጋር ያለቋንቋ ችግር እርስ መግባባት የሚችሉበትን መንገድ መፍጠር ተችሏል።

በዚህም አፋርኛ ተናጋሪው የሎጊያ ሰው ከሶማሌኛ ተናጋሪው የጎዴ ሰው ጋር፣ ትግርኛ ተናጋሪው የመቐለው ሰው ደግሞ ከአማርኛ ወይም ከሌላው ቋንቋ ተናጋሪ ጋር ቴክኖሎጂውን ብቻ ተጠቅሞ ሶስተኛ ሰው ሳያስገቡ መግባባት ይችላሉ። በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን ከጽሑፍ ወደ ድምፅ የመቀየር እና ድምፁን ወደ ጽሑፍ የመቀየር ሥራም በኤአይ እየተሠራ ነው።

ለወጣቶች ተስፋ የሰነቀ ሥራ

ከዚህ ሁሉ የኢንስቲትዩቱ የሚመነጨው ቁም ነገር፣ ሰው የጠራ ራዕይ ኖሮት በከፍተኛ ዲሲፕሊን መሥራት ከቻለ አንድን ነገር ባየው ልክ ማሳካት እንደሚችል እና ኢትዮጵያም ብቃት ያላት ሀገር መሆኗን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንሥተዋል።

በተለይ የባህር ውስጥም ሆነ የተለያዩ የምናባዊ ምሥሎችን ዕውነተኛ አስመስሎ የሚያቀርበውን የ‘ኢመርሲቭ ቴክኖሎጂ’ ልምድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለወጣቶች ማቅረብ ተችሏል። ይህንን እያዩ የሚያድጉ ወጣቶች ፈጠራቸው ከፍተኛ እንደሚሆን አያጠራጥርም።

በተጨማሪ በስታርት አፕ  ምኅዳር ወጣቶች ሐሳባቸውን ወደተሟላ ፕሮጀክት የሚቀይሩበት ማዕከል እና ከውጭ ኢንዱስትሪ ጋር የሚገናኙበት መድረክ የሚፈጥር ሥርዓት በኢንስቲትዩቱ ተዘርግቷል። ይህም ለበርካታ ወጣቶች ትልቅ ዕድልን ያመጣል፤ እችላለሁ የሚል መንፈስንም ያዳብራል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳነሡት፤ አፍሪካ ትችላለች፤ የኢትዮጵያ ወጣትም በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ታግዞ ዓለምን የሚቀይር ሥራ መሥራት ይችላል!

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ አብዮት እና በሌሎች ጉዳዮች ያጋጠማት መዘግየት በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስም እንዳይደገም “ከመዘግየት ወደ ተስተካካይነት” በሚል መርሕ ከዓለም ጋር አብሮ የመጓዝ ሂደቱን ጀምራለች።

በጌትነት ተስፋማርያም

#EBC #Ethiopia #PMAbiy #EAII #AI