Search

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ምን ያህል ዘመናዊና ግዙፍ ተቋም ነው?

ማክሰኞ ኅዳር 09, 2018 181

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመረቀው የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ዋና መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ላይ ትልቅ እመርታን የሚፈጥር ዘመናዊ ተቋም መሆኑ አያጠራጥርም።

ዓለም በደረሰበት ቴክኖሎጂ የተደራጀው ይህ ግዙፍ ተቋም 15 ሚሊየን ጊጋ ባይት ወይም 15 ፔታባይት የሚሆን መረጃን የማከማቸት አቅም ያለው የዳታ ሴንተር በውስጡ ያካተተ ነው።

የዚህን ግዙፍ ዳታ ሴንተር መጠን ለማስረዳት ያህል ይህ ዳታ ሴንተር እያንዳንዳቸው 200 ገፅ ያላቸው ከ 70 ቢሊየን በላይ ዲጂታል መፅሀፍትን መያዝ የሚችል አቅም ያለው ነው እንደማለት ነው።

ወይም እያንዳንዳቸው 3 ሜጋ ባይት መጠን ያላቸው ከ5 ነጥብ 35 ቢሊዮን በላይ ብዛት ያላቸው ዲጂታል ፎቶዎችን አሊያም ደግሞ እያንዳንዳቸው 4 ሜጋ ባይት መጠን ያላቸው 4 ነጥብ 2 ቢሊየን በኤምፒ 3 (mp3) የተዘጋጁ የድምፅ ፋይሎችን ወይም ሙዚቃዎችን መያዝ የሚችል አቅም ያለው ዳታ ሴንተር ነው።

ዘመኑ የደረሰበትን የስማርት ህንጻ ቴክኖሎጂ መሰረት በማድረግ እንደ አዲስ የተደራጀው የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢኒስቲቲዩት ባለ 15 ወለል ህንጻ ከውጫዊው ጀምሮ እስከ ውስጣዊ ይዘቱ እጅግ በዘመነ መልኩ ስያሜውን በሚመጥን ደረጃ የተሰራ ነው።

በዚህም መሰረት የህንጻው ክፍሎች በሙሉ ስማርት መስታወት የተገጠመላቸው ሲሆን እነዚህ መስታወቶች በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ከኮምፒውተሮች ጋር ተገናኝተው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት የፀሀይ ጨረርን እና የክፍሎቹን ብርሀን መቆጣጠር የሚችሉ ናቸው።

ይህም የኤሌትሪክ ፍጆታን ከመቀነሱም በላይ ምቹ የሆነ የስራ አካባቢን የሚፈጥር ሆኗል።

በተለያዩ የህንጻው ክፍሎችም የምርምርና የጥናት ቢሮዎች፣ ዓለም የደረሰበትን የAI ቴክኖሎጂ የያዘ የስልጠና ማዕከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመማሪያ መጻህፍትን የያዘ ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍትን አካቷል።

እንዲሁም የሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የምርምርና ውጤቶች ማሳያ አዳራሽ እና በርካታ አገልግሎት መስጫዎችንም በውስጡ ያካተተ ነው።

በዋሲሁን ተስፋዬ

#EBC #Ebcdotstream #Ethiopia #PMAbiy #EAII #AI