በሴራ ከነበራት የባሕር በር የተገለለችው ኢትዮጵያ፣ ከዚያ በኋላ ባለፉት ዓመታት አጀንዳውን በሀገር ውስጥም ሆነ በቀጣናው አካባቢዎች ማንሳት እንደ ነውር ይቆጠር እንደነበር የፖለቲካ ተንታኞቹ አቶ ዘሪሁን ተሾመ እና አቶ አፈወርቅ በደዊ በኢቲቪ የሀገር ጉዳይ ፕሮግራም ላይ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓትም ቢሆን ከ1997ቱ ሀገራዊ ምርጫ በኋላ አጀንዳውን ማንሳት የማይሞከር እና ጉዳዩ እንደተዘጋ ሆኖ በመታየቱ፣ የባሕር በር ጉዳይ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ አጀንዳ ተገፍቶ መቆየቱን ተንታኞቹ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ስታጣ የነበራት የሕዝብ ቁጥር በአሁኑ ሰዓት ከእጥፍ በላይ ያደገ ሲሆን፣ በቀጣይ ጊዜያትም ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ አስተማማኝ የባሕር በር የሚያስፈልጋት ጊዜ ላይ ደርሳለች ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ እየሆነ የመጣው የቀይ ባሕር ቀጣና ላይ 12 የሚሆኑ የዓለም ሀገራት የጦር ሰፈር በመሰረቱበት በዚህ ወቅት፣ ከቀይ ባሕር 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷ የሚያስቆጭ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያነሱት የባሕር በር ጥያቄም ጊዜውን የጠበቀ ነው ያሉት ተንታኞቹ ፤ አሁን ያለውም ትውልድ አላማውን ደግፎ መቆም እንዳለበት አመላክተዋል።
ይህን አጀንዳ መደገፍ ጦረኛ አያስብልም፤ የሚያሽኮረምምበት ጊዜም አብቅቷል ሲሉም ተንታኞቹ ገልፀዋል።
አንዳንድ የባሕር በር ጥቅም ያልገባቸው አካላት "ወደብ ተከራይተን በሰላም መጠቀም እንችላለን" ይላሉ፤ ኢትዮጵያ ያነሳችው ጥያቄ ግን የሉዓላዊነት ጥያቄ በመሆኑ የባሕር በር እና ወደብ ደግሞ ይለያያሉ።
የባሕር በር ካለ ደግሞ ወደብ እንደሚኖር የታወቀ ነው ያሉት ተንታኞቹ የባሕር ኃይል ያቋቋመች ሀገር የግድ የራሷ የባሕር በር ያስፈልጋታል ሲሉ አንስተዋል።
በሃብተሚካኤል ክፍሉ