(የዕለቱ መልዕክት)
ባለፉት ስምንት ዓመታት ኢትዮጵያ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ያስመዘገበቻቸው ጉልህ ሥራዎች የነገዋን የበለጸገች ሀገር መልክ እና ግብ የወሰኑ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው።
ሀገርን የመገንባት ሂደት የጋራ ማንነትን፣ ዘላቂ ሰላምን እና የኢኮኖሚ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የሚደረግ ሁሉን አቀፍ እና ተከታታይ የትብብር ጉዞ በመሆኑ፣ በእነዚህ ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ለሀገራችን ሕልውና እና ከፍታ አዲስ መሠረት ጥለዋል።
ይህ ጉዞ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመፍጠር ፍትሕን፣ አስተዳደርን እና የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቁ ተቋማትን የመገንባት ሥራን ያካተተ ነው።
እነዚህ ሕዝባዊ ተዓማኒነት ያላቸው ጠንካራ ተቋማት ሀገርን በዘላቂነት ለማስተዳደር እና አስተማማኝ ዋስትና ለመስጠት የሚያስችሉ ዋነኛ ምሰሶዎች ሆነዋል።
የከተሜነት መስፋፋት እና የኢኮኖሚ ዕድገት ለሀገር ግንባታ ያላቸው ቁርኝት ከፍተኛ እንደመሆኑም መጠን ከተሞች የሀገር ኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ መስተጋብር እና የቴክኖሎጂ ማዕከል በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ታከናውናለች በተሰኘው ብሔራዊ ጉባኤ ላይ እንደገለጹት፣ ሀገራችን በራሷ አቅም ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት እና ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ ግዙፍ ልማቶችን በማከናወን በየጊዜው ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረች ትገኛለች።
እነዚህ ሁሉ ስኬቶች በአጋጣሚ የተገኙ ድሎች ሳይሆኑ በመደመር መንፈስ ላይ ተመሥርተው "ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው በጋራ በመቆም ነው" በሚል ጽኑ እምነት ከተወሰዱ ቆራጥ ውሳኔዎች የተገኙ የጋራ ውጤቶች ናቸው።
አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የሆነች ሀገር የመገንባት ራዕይን ከግብ ለማድረስ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ዕቅዶች ሳይቆራረጡ ተግባራዊ መደረግ ይኖርባቸዋል።
የተመዘገቡት ስኬቶች በራሳቸው የመጨረሻ ግብ ሳይሆኑ ከእኛ በኋላ ለሚመጡት ተከታታይ ትውልዶች የምንጥለው ጠንካራ መሠረቶች ናቸው።
ሀገርን መገንባት በአንድ ትውልድ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን የሁላችንም የጋራ እና ቀጣይነት ያለው ሥራ በመሆኑ የጀመርናቸውን የለውጥ ጉዞዎች ዘላቂነት ማረጋገጥ የወቅቱ ዋነኛ ጥሪ ነው።
ሐሳብ ለአስተሳሰብ ግንባታ መሠረት እንደመሆኑ መጠን ዛሬ በአዕምሮአችን የምንቀርጸው ማንኛውም እሳቤ የነገዋን ሀገር ዕጣ ፈንታ ይወስናል።
ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህንን የጋራ ሀገር የመገንባት መንፈስ ይዞ ወደፊት ሊጓዝ እና ከተረከበው ታሪካዊ አደራ በላይ አግዝፎ ሀገሩን ወደ ላቀ ከፍታ ሊያመራት ይገባል።
ዛሬ የምንከፍለው መሥዋዕትነት እና የምናሳየው ቆራጥነት የነገዋን ጠንካራ፣ ኩሩ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረጊያ ብቸኛው መንገድ ነው።
የኢቢሲዶትስትሪም ኤዲቶሪያል