Search

ፆም ያላደረው መሬትና የለመለመው ተስፋ፦ የግብርናዉ የለውጥ ጉዞ

ረቡዕ ሰኔ 17, 2018 72

 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዘመናት ከድህነት አዙሪት መውጣት ያልቻለው የምርት ሂደቱ ከዝናብ ጥገኝነት እና ከኋላቀር አሠራር ባለመለቀቁ እንደነበር ይታወቃል።

ይህንን ታሪካዊ ስብራት ለመጠገን ባለፉት 8 የለውጥ ዓመታት የተከናወኑት የግብርና ዘርፍ ማሻሻያዎች  የሀገራችን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መልክ የቀየሩ እና የዜጎችን ክብር ከፍ ያደረጉ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች ናቸው።

መንግሥት ግብርናውን ከልመናና ከችሮታ ጥገኝነት አውጥቶ የኢኮኖሚው ዋና ሞተር ለማድረግ የወሰደው ቁርጠኝነት፣ በሀገራችን  አዲስ የታሪክ እጥፋት ፈጥሯል።

ይህ ትራንስፎርሜሽን የገጠሩን ማኅበረሰብ ሕይወት ከመቀየር ባለፈ የኢንዱስትሪያላይዜሽንና የሀገራዊ ብልፅግናን መሠረት ጥሏል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የታየው ትልቁ ስኬት ግብርናን በቴክኖሎጂ በመደገፍ አርሶ አደሩን ወደ ገበያ-ተኮር ምርት ማሸጋገር መቻሉ ነው።

ይህም በቁጥር የታገዙ ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡበት ማሳያ ሆኗል። ለምሳሌ በ2013 በጀት ዓመት 17.2 ሚሊዮን ሄክታር የነበረው የታረሰ መሬት፣ በ2017 በጀት ዓመት ድግግሞሽን ጨምሮ ወደ 32.2 ሚሊዮን ሄክታር አድጓል።

ይህ የመሬት አጠቃቀም ስፋት በተለይም "የትኛውም መሬት ፆም አያድርም" በሚል መርህ በተሰራዉ ስራ ፣ አጠቃላይ የሰብል ምርትን ከ356.6 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 836.4 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያድግ አድርጎታል።

በ2017 ዓ.ም የምርት ዘመን አጠቃላይ የግብርና ምርት 1.57 ቢሊዮን ኩንታል መድረሱ የዚሁ የተቀናጀ ጥረት ፍሬ ነው።

ከምርት ዓይነቶች አንጻር ሲታይ የስንዴ ምርት በየዓመቱ የ49 በመቶ አስደናቂ ዕድገት በማሳየት ኢትዮጵያ  የምግብ ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥና ስንዴን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንድትችል አድርጓታል።

ከዚህ በተጨማሪ የሩዝ ምርት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 63 ሚሊዮን ኩንታል፣ የቡና ምርት ደግሞ ወደ 11.5 ሚሊዮን ኩንታል በማደጉ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።

ይህ ስኬት ግብርናው የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ግብዓትን በሀገር ውስጥ ለመተካትና ለውጭ ገበያ ጥራት ያለው ምርት ለማቅረብ ያስቻለ ጠንካራ መሠረት ሆኗል።

ከሰብል ምርት ባሻገር፣ መንግሥት ይፋ ያደረገው "የሌማት ትሩፋት" መርሃ-ግብር በእንስሳትና በእንስሳት ተዋጽኦ ምርት (ወተት፣ ዶሮ፣ ማርና ዓሳ) ረገድ ተምሳሌታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

ይህም የሥነ-ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጡም በላይ የዜጎችን የኢኮኖሚ ነፃነት እያገዘ ነው።

በተመሳሳይ መልኩ የከተማ ግብርና  የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም፣ የከተሞችን ገጽታ ለመቀየር እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የጓሮ ሜዳዎችን  ወደ ምርታማነት በመቀየር አዲስ ባህል ፈጥሯል።

የነገው የብሩህ ጉዞ መሠረት የሆኑት እነዚህ ውጤቶች ወደፊትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ  ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ግብርናን ማዘመንና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል።

በመስኖ አቅምን በማጎልበት ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት የማላቀቅ ሥራ በስፋት የሚቀጥል ሲሆን "ከእርሻ እስከ ጉርሻ" ያለውን የዕሴት ሰንሰለት ለማዘመን ዲጂታል ቴክኖሎጂንና ሜካናይዜሽንን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል ታቅዷል።

ከዚህም በላይ መንግሥት የጀመረውን የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በማጠናቀቅ ቁልፍ የግብርና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆኑ  የዘርፉን ዘላቂነት አስተማማኝ ያደርገዋል።

ባጠቃላይ ባለፉት 8 ዓመታት የተከናወኑት የለዉጥ ሥራዎች ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ አምራችነት፣ ከምግብ ዋስትና እጦት ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማሸጋገር የተገባውን ቃል በተግባር ያረጋገጡ የታሪክ አውታሮች ናቸው።

በበረከት ሽመልስ