Search

የኢትዮጵያ ማንሰራራት፡ እንዴት ወዴት?

ረቡዕ ሰኔ 17, 2018 82

 

"ማንሰራራት" የሚለው ቃል ከውድቀት፣ ከድካም ወይም ከረዥም እንቅልፍ በኋላ አዲስ ኃይል አግኝቶ መነሳትን፣ መታደስን እና በድል አድራጊነት ዳግም መገንባትን ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የኢትዮጵያ ማንሰራራት" ሲሉ፣ ሀገራችን ለዘመናት ከነበረችበት የኋላቀርነት፣ የድህነትና የግጭት አዙሪት ወጥታ፣ አሁን ላይ በተግባር ወደምታሳየው ሁለንተናዊ የብልጽግና እና የሉዓላዊነት ዳግም መነቃቃት መሸጋገሯን ለማብሰር ነው።

ይህ "ማንሰራራት" ከቀድሞው ዕሳቤ መነሳት እና ህዳሴ ከሚለው ጽንሰ-ሀሳብ የሚለየው፣ መነሳት ምኞትንና ጅምርን ሲያሳይ፣ ማንሰራራት ግን ተጨባጭ ፈተናዎችን ተሻግሮ፣ ስብራቶችን ጠግኖ በጠንካራ መሠረት ላይ ዳግም መቆምን ስለሚወክል ነው።

የዚህ ማንሰራራት አንዱና ዋነኛው መገለጫ "መፍጠር፣ መፍጠንና መዝለል" (To leap, not to catch up) በሚለው መደመራዊ የኢኮኖሚ ስልት ውስጥ ይገኛል።

አዳጊ ሀገራት የበለጸጉትን ሀገራት የዘመናት ጉዞ ደረጃ በደረጃ ለመድገም የቅንጦት ጊዜ የላቸውም። በመሆኑም ኢትዮጵያ አዝጋሚውን ጉዞ በመዝለል በቀጥታ ወደ ዘመናዊው የዲጂታል እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ገብታለች።

የ"ፋይዳ" ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ እና በመሶብ በኩል የሚሰጡ የኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች፣ ዜጎችን ከማግለል ወደ አካታችነት ያሸጋገሩ የማንሰራራቱ ዲጂታላዊ አሻራዎች ናቸው።

በግብርናው ዘርፍ የሚታየው ተዓምራዊ ለውጥ የኢትዮጵያን ማንሰራራት በጉልህ የሚያሳይ ሌላው አስረጂ ነው። ከዝናብ ጥገኝነት ወጥቶ በመስኖ፣ በሜካናይዜሽን እና በኩታ ገጠም እርሻ በተሰራው ሰፊ ሥራ፣ ኢትዮጵያ የዘመናት የስንዴ አስመጪነት ታሪኳን ቀይራ ወደ ላኪነት መሸጋገሯ የማንሰራራቱ ትልቁ ድል ነው።

የ"ሌማት ትሩፋት" ሀገራዊ ፕሮግራምም እንዲሁ የዜጎችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ሀገሪቱን ከተረጂነት ሥነ-ልቦና ወደ አምራችነት እያሸጋገራት ይገኛል።

"የምትተክል ሀገር፣ የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል ላለፉት ሰባት ዓመታት የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርም የኢትዮጵያ ማንሰራራት የህያውነት መገለጫ ነው።

ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ፣ የደን ሽፋን ከ23 በመቶ በላይ እንዲደርስ እና ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ (COP32ን እስከማዘጋጀት) ግንባር ቀደም ተዋናይ እንድትሆን አድርጓታል።

ይህ ኢትዮጵያ ከውስጥ ተፈውሳ ለዓለም መትረፍ መጀመሯን ያሳያል።

በዲፕሎማሲውና በጂኦ-ፖለቲካው መስክም ኢትዮጵያ እያንሰራራች ነው።

የBRICS አባል መሆኗ፣ ለዘመናት ታፍኖ የነበረውን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በድፍረት ወደ ጠረጴዛ ማምጣቷ፣ እና የሕዳሴ ግድብን የውጭ ጫናዎችን ተቋቁማ በስኬት ማጠናቀቋ ሀገሪቱ ከስልታዊ ኩስመና ወደ ስልታዊ ሉዓላዊነት (Strategic Autonomy) መሸጋገሯን የሚያረጋግጡ ናቸው።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ማንሰራራት የፖለቲካ ንግግር ብቻ ሳይሆን፣ የተበላሹ ተቋማትን በማደስ፣ ኢኮኖሚውን ከዕዳ ወደ ምንዳ በማሸጋገር፣ እና የብዙሃንን ድምፅ በማስተናገድ የተገኘ የጋራ ትሩፋት ነው።

ይህ ማንሰራራት ትናንትን በይቅርታ፣ ዛሬን በትጋት፣ ነገን ደግሞ ለቀጣዩ ትውልድ በጽኑ መሠረት ላይ በማስረከብ የኢትዮጵያን ዘላቂ ልዕልና የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ጉዞ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ