Search

የዓለምን ትኩረት ያገኘው የኢትዮጵያ ሥራ

ረቡዕ ኅዳር 10, 2018 728

ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያዎችን በመከተል የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት ፤ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል እየሠራች ይገኛል።

በአፍሪካ አህጉር የማኅበረሰብና አካባቢ ጤናን ለመጠበቅ በቅድመ መከላከል ረገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች የዓለምን ትኩረት እየሳቡ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርቶች መሰረት፣ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የግልና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።

ኢትዮጵያም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደመሆኗ፣ በዚህ ዘርፍ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ፖሊሲ አውጥታ በከተማና በገጠር ተግባራዊ ሥራዎችን እየሠራች መሆኑም ተመላክቷል።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ፣ ኢትዮጵያ በሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የምትሠራው ሥራ የተሻለ ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው። አሁንም ግን ለበርካታ የማኅበረሰብ ክፍል ንጹሕ የሕዝብ መፀዳጃ ቤትን ማዳረስ እንደሚገባ ተመላክቷል

የግልና አካባቢ ንፅህና ችግር ከሥር መሠረቱ ለመቅረፍ መንግሥት ከገጠርና ከከተማ ኮሪደር ልማቶች ጎን ለጎን ዘመናዊ የሕዝብ ሽንት ቤቶችን በመገንባት በስፋት እየሠራ ይገኛል።

በመዲናዋ አዲስ አበባ በአንድ ጀንበር በተደረገ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ፣ በመንገድ ዳርቻዎች፣ በብዙኃን ትራንስፖርት ማሳለጫዎች፣ በመናኸሪያዎችና ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች ዘመናዊ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ተገንብተዋል። ይህ ሥራ ወደ ክልሎች ከተሞችና ገጠር መንደሮችም እየተስፋፋ ነው።

የሕዝ መፀዳ ቤቶችን ግንባታ ለማከናወን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካኝነት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር በጀት መድበው እየሠሩ ነው።

በገጠርም ሞዴል መንደሮችን ለመፍጠርና ለማስፋት በሚደረገው ጥረት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች ተገንብተው ለማኅበረሰቡ ማሳያ እየሆኑ ነው።

በአፍሪካ አህጉር ቱኒዚያ የአካባቢ ብክለትን ለማስቀረት የገጠርና ከተማ የማኅበረሰብ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት በመዘርጋት፣ 90 በመቶ የማኅበረሰብና የአካባቢ ንጽህና በመጠበቅ በአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ሲሼልስ 98 በመቶ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት ብቻ ሳይሆን፣ በደሴቶቿና በውኃ አካላት ላይ የሚደርስ ብክለትን ለማስቀረት የሚያስችል መሠረተ ልማት በመዘርጋት ምርጥ ተሞክሮ ያላት ሀገር ሆናለች።

ጋና፣ ሴኔጋልና ሩዋንዳ የማኅበረሰብ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታን በመንግሥት ደረጃ ብሔራዊ ፕሮግራም አውጥተው፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ዘርግተው እየሠሩ ያሉ ሀገራት ናቸው።

ኢትዮጵያየዓለም ጤና ድርጅት መመሪያዎችን በመከተል የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በስፋት በመገንባት ረገድ ጥሩ ጅምር በማሳየቷ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እየተቸራት ይገኛል።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዓለማችን 3.5 ቢሊዮን ዜጎች ዛሬም ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቤት የላቸውም።

በመሀመድ ፊጣሞ