Search

በተጨባጭ ውጤቶች የታጀበው የኢትዮ-ሳዑዲ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

ሓሙስ ኅዳር 11, 2018 81

የኢትዮ-ሳዑዲ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እና በተጨባጭ ውጤቶች የታጀበ ነው ሲሉ በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያና ሳዑዲ ዓረቢያ ዘመናትን የተሻገረ የባሕል፣ የኃይማኖትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዳላቸው አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ቅርጽ የያዘው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት አሁን ላይ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ማህበራዊ መስተጋብር እያደገ መምጣቱን ነው ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ ከለውጡ ወዲህ የሀገራቱ ሁለንተናዊ አጋርነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ማደጉን ጠቁመው፤ በዚህም በርካታ የሳዑዲ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ የግብርና ምርቶችን ወደ ሳዑዲ እንደምትልክ ተናግረው፤ የሁለቱ ሀገራት ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን ገልጸዋል፡፡
በሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት በርካታ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ማድረግ መቻሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ 200 ሺህ ኢትዮጵያውያንን በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገሪቱ መግባታቸውን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት 360 ሺህ ዜጎችን ለመላክ እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
በቀጣይም የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩንና ሁለንተናዊ ግንኙነትን የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡