የግብርና ምርቶችን ስናመርት ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት ላይ ትኩረት በማድረግ ነው ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።
አቶ ላጫ ይህን ያሉት 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በዞኑ የልማት ሥራዎች እና የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ምልከታ ሲያደርግ ለቆየው የጋዜጠኞች ቡድን መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።
ዋና አስተዳዳሪው በመግለጫቸው፥ በዞኑ የእርሻ ሥራ በመኸር፣ በበልግ፣ በፀደይ እና በመስኖ እንደሚከናወን እና በዚህም የተለያዩ የግብርና ምርቶች እንደሚመረቱ ገልጸዋል።
በፀደይ ወራት ከመስከረም እስከ ጥቅምት አጋማሽ የበቆሎ ምርት ተሰብስቦ ሲያበቃ በዚያው ማሳ ላይ ሽንብራን ጨምሮ በእርጥበት ብቻ ሊበቅሉ የሚችሉ ምርቶች እንደሚመረቱ ተናግረዋል።
ይህ የፀደይ እርሻ ሥራ የተጀመረው በዞኑ በአበሽጌ ወረዳ ባለፈው ዓመት መሆኑን ጠቅሰው፤ በወረዳው በ24 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሽንብራ መመረቱን አክለዋል።
በተያዘው የምርት ዘመንም በአበሽጌ ወረዳ በቆሎ የተነሳበት ማሳ 31 ሺህ ሄክታር መሬት በሽንብራ ዘር ተሸፍኗል ያሉት አቶ ላጫ፤ ከዚህ ቀደም በቆሎ የተነሳበት ማሳ ቢያንስ እስከ በልግ ድረስ ጦሙን ያድር እንደነበር አስታውሰዋል።

በዞኑ ከዚህ ቀደም ያልተለመዱ የምርት ዓይነቶች እየተመረቱ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ለአብነትም ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሮዝመሪ ምርት እንደተሸፈነ ተናግረዋል።
መንግሥት አሁን ላይ የሮዝመሪ ምርትን ለውጭ ገበያ እያቀረበ ነው ያሉት አቶ ላጫ በዞኑ እየተመረተ ያለው የሮዝመሪን ምርትም ለውጭ ገበያ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አሁን ላይ ዞኑ ሮዝመሪን ጨምሮ የግብርና ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያም እያቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ዞኑ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠው ትልቅ ትኩረት የአፈር እና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የጠረጴዛማ እርከን ሥራን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዞኑ ለኢንቨስትመንት ምቹ ነው ያሉት ኃላፊው ግብርና እና ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ የዞኑ አስተዳደር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በሃይማኖት ከበደ
#ebcdotstream #centralethiopia #guragezone #agriculture