3ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ዓመታዊ የአየር ንብረት ለውጥ የጋዜጠኞች ሽልማት ሥነ-ሥርዓት የፊታችን ኅዳር 20 እና 21 በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገለፀ።
ኢጋድ ከኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሚያካሂደው ፕሮግራም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተሰሩ እጩ ዘገባዎች ተመርጠው ይሸለማሉ።
በዚህም ከአህጉሪቱ ከ400 በላይ ጋዜጠኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ 94 ዘገባዎች መካተታቸውን በኢትዮጵያ የኢጋድ ተወካይ አበባው ቢሆነኝ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራን እንዲሁም የታዳሽ ኃይልን በማስፋፋት ረገድ በሰራችው ውጤታማ ተግባር መርሀ-ግብሩን እንድታዘጋጅ ተመርጣለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገልፀዋል።
ለሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ከተለያዩ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጋዜጠኞችም የተለያዩ ቦታዎችን የሚጎበኙበት ዕድል ተመቻችቷል ብለዋል።
በ8 ዘርፎች በሚካሄደው ውድድሩ ላይ አሸናፊ ለሚሆኑትም የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል ተብሏል።
ዓመታዊው የኢጋድ የሚዲያ ውድድር ከዚህ ቀደም በጅቡቲ እና በኬንያ የተካሄደ ሲሆን፣ ቀጣይ ዓመት በኡጋንዳ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በቶማስ ሀይሉ