የኒውክሊየር ኃይል ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለጀመረችው ጉዞ አስተማማኝ አቅም እንደሚፈጥርላት የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን ገለፀ።
የተቋሙ ምክትል ኮሚሽነር አብዱራዛቅ ኡመር (ኢ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኒውክሊየር ኃይል የኢትዮጵያን የዕድገት ሽግግር የሚያረጋግጥ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ለማቅረብ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ኒውክሊየር ኃይል ልማት ለመግባት የወሰነችው ትልቅ ሀገር እንደመሆኗ መጠን የኢንዱስትሪ ጉዞዋን እንዲሁም የኢኮኖሚ እድገቷን በአስተማማኝ ኃይል ለመደገፍ በማለም ነው ብለዋል።
ዘርፉ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታም ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት ፋይዳ ያላቸው በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።
የኒውክሊየር ኃይል ፕሮግራም የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አበረታች ውጤቶችን እያመጣች መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኒውክሊየር ኃይል ኮሚሽን በቅርብ ጊዜ መቋቋሙን ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ተቋሙ ችግር ፈቺ የሆኑ የቴክኖሎጂ እቅዶችን በመንደፍ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።
በሜሮን ንብረት