በጃፓን ቶኪዮ በሚገኝ ሬስቶራንት ሊመገቡ ገብተው ቸኩለው ዓሳ ወይንም በአካባቢው የተለመደውን ሱሺ ቢያዙ ያላዘዙት ጥብስ ወይ ሌላ ምግብ ሊመጣልዎት፤ አልያም ያዘዙት አስተናጋጅ እሱንም ዘንግቶ ውሃ ብቻ ይዞ ሊመጣልዎት ይችላል።
አያርገውና በውሃ ጥም ተቃጥለው እባክህ ውሃ አምጣልኝ ብለው ቢያዙ ለደቂቃዎች ውሃው ሊዘገይና ጨርሶም ሊረሳ እንደጠማዎት ሊቆዩ ይችላሉ።

በዚህ ሬስቶራንት ያላዘዙትን ምግብ ማምጣት፤ የታዘዙትንም መርሳት ለአስተናጋጆቹ የተፈቀደ በተስተናጋጅም የተለመደ ነው።
የሬስቶራንቱ መጠሪያ በራሱ የተሳሳቱ ትዕዛዞች የሚቀርቡበት ሬስቶራንት "RESTAURANT OF MISTAKEN ORDERS ይሰኛል፡፡"
በዚህ መሳሳት አስተናጋጆቹን ያስቀጥራል እንጂ አያስባርርም፤ ተስተናጋጆችም ከንዴት ይልቅ እጅግ ደስተኛ ሆነው ያላዘዙትንም ተጠቅመው በደስታ ይወጡበታል እንጂ ሲያማርሩ በጭራሽ አይሰማም።

ይህ ተሞክሮ ሲንጋፖርን ጨምሮ በሌሎች ሃገራት ተወስዶ ተመሳሳይ ስህተትን የሚፈቅዱ ሬስቶራንቶች እንዲከፈቱም ምክንያት የሆነ ነው።
ይህ እንዴት ይሆናል? በእንደዚ ዓይነት ሬስቶራንቶችስ ምን ዓይነት ሰው ይጠቀማል? ቢሉ ታዲያ የሌሎችን ስህተት ለመቀበል ክፍት የሆነ አዕምሮ ያላቸው ብቻ ነው መልሱ።
ሬስቶራንቱ የተከፈተው በመርሳት በሽታ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖር ታልሞ ነውና ለመስተንግዶ የሚቀጠሩትም የመርሳት በሽታ የጠናባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው።

ለወትሮው በዚህ ዓይነት የመርሳት በሽታ የተጠቁ ሰዎች በማህበረሰቡ መገለል ይደርስባቸዋል።
ይህም ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋቸዋል የሚለው የሬስቶራንቱ መስራችና በመደበኛ ሙያው የቴሌቭዥን ዳይሬክተሩ ሺሮ ኦጉኒ ነው።
በእርጅናም ሆነ እርጅናን ተከትሎ በሚመጣው የመርሳት ችግር ላይ ለመስራት አልሞ ነው ይህን ፕሮጀክት ወደ ቢዝነስ ቀይሮ የመሰረተው።
ይህን አስተሳሰብ ለመቀየርና ለተጠቂዎቹ እንከን እንዳልሆነ አምነው በተስፋ እንዲኖሩ፤ ሌላው ሰውም ይህን እንደችግር ከመቁጠር ይልቅ ሰዎቹን ቀርቦ ለመረዳትና ለመውደድ የሚያስችለውን ዕድል መፍጠር በተግባር ያሳየበት ፕሮጀክት ሆኗል።
እናም በዚህ ሬስቶራንት ከምግብ ይልቅ የሰው ፍቅር በገፍ ይሸጣል ቢባል ምንም ግነት የለውም።
በዓለማችን በዕድሜ የገፉ ሰዎች ብዛት ቀዳሚ እንደሆነች የሚነገርላት ጃፓን ከዕድሜ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ በሽታዎች አንዱ በሆነው የመርሳት በሽታ የተጠቁ ብዙ ዜጎች ያሉባት ሀገር ነች።
በዓለም ላይ 35 ሚሊዮን የሚሆነው ሰው ደረጃው ቢለያይም በመርሳት ችግር ተጠቂ እንደሆነና በ2050 ይህ ቁጥር ወደ 115 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብም ይጠበቃል።
የሬስቶራንቱ ባለቤት እንደሚለውም ማህበረሰቡ ስለመርሳት በሽታ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና የችግሩ ተጠቂዎችንም መረዳትና በፍቅር አብሮ መኖር የሚችለው በዚህ ዓይነት መንገድ መቀራረብ ሲችል ነው ይላል።
ታዲያ ያዘዙትን ቢረሱም ብዙ ፍቅር ለሚሰጥዎት አስተናጋጆች እርስዎም የሚሰጡት ትልቁ ክፍያ ፍቅር ነው፤ በፍቅር ያቆየን።
በአክሱማዊት ገብረ ሕይወት