Search

ከቤተሰቧ የነጠላት ሙዚቃን የነፍሷ ትርታ ያደረገችው ድምጻዊት ዛሬም በይቅርታ ደጃፍ ላይ ቆማለች

ረቡዕ ኅዳር 17, 2018 62

የባህል ተብሎ በተዘጋጀ የትኛውም ዐውድ አትታጣም።  በተለይ የብሄር ብሄረሰብ ቀን ሲከበርም ሆነ ከህዳር አጋማሽ አንስቶ በሚከበረውና ታህሳስ 1 ፍጻሜው በሚሆነው የድሽታ ግና የዘመን መለወጫ በዓል እርሷን ከመሃል ማጣት ይከብዳል።

የአሪ ብሄረሰብ ተወካይ፣ ድምጻዊትና ተወዛዋዥ ሆና ለረዥም ዓመታት እያገለገለች የምትገኘው ዙፋን አወቀ አሁን በአዲስ አበባ ራዊ ቴአትር እና በተለያዩ የባህል ቤቶች እየሰራች ትገኛለች።

ተወልዳ ካደገችባት የአሪዋ ሸንጋማ ቢሊም በአጭር ጊዜ ወደጂንካ ከዛም ወደሃዋሳ አቅንታ የባህል ኪነቶች ውስጥ አገልግላለች። የኪነ-ጥበብ ፍቅርም ስጦታም እንዳላት በዙሪያዋ ያሉ የተረዱላት ግን ገና በልጅነት ነበር።

ዙፋን በአካባቢዋ እንዳሉ እንደሌሎች ሴቶች ሁሉ ያለዕድሜዋ ተድራ ብዙ ውጣ ውረድ ገና በልጅነት ልትጋፈጥ ግድ ሆነ። የምታልፍበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ትረዳ ነበርና መብቷን በቻለችው መጠን ለማስከበር ታግላለች። እርሷ ያለፈችበት ፈተና  በእርሷ እንዲበቃ ስለሌሎች ሴቶች የነጻነት መንገድ ፍለጋ ቀጠለች።

ሙዚቃም  ቁጭቷን ለመተንፈስና ስለሌሎች ለመታገል ዋና መንገድ ሆናት። የመጀመሪያ ስራዋም አዲስ ተስፋን ያበሰረችበት አይዞሽ አይዞን አልፏል ነግቷል ያለችበት በልጅነት ዋጋ ለከፈሉ ሴቶች መታወሻ የሰራችው 'መዬ ጋይሴ' (ወጋገን ) ነበር።

ዙፋን ከምትታወቅባቸውና ለየት ካሉ የራሷ የሙዚቃ ስራዎች አንዱ መዬ ጋይሴ ከምትወደውና ከምታደንቀው ክፍሌ ወሰኔና ተስፋዬ ጋይሴ ጋር በጋራ የሰራችበት ነው። በጎጂ ልማዳዊ ድርጊትና በተለያዩ ጾታዊ ጥቃት ላለፉ ሴቶች መታሰቢያነት የሰራችው ልዩ ስራዋ እንደሆነም ትናገራለች። ግጥምና ዜማውም ጭምር የእርሷ ነው። ቀጥላ ደግሞ ስለአሪ ብሄረሰብ ድል ያቀነቀነችበት ሙዚቃዋን ሰራች።

ግጥም የራሷ፤ ዜማው የህዝብ የሆነው ሶስተኛው ስራዋ 'ወኒዬ' ነው። 'አሪ አንበሳ ' የምትልበት። ከእነዚህ ስራዎቿ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣትም ሌላኛው አበርክቶዋ በኮቪድ ጊዜ የተሳተፈችበት የጋራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሙዚቃ  በግጥምና ዜማ እንዲሁም በድምጽ የተሳተፈችበት ሌላኛው ስራዋ ነው። ለመጨረሻ ጊዜም ፕሮዲዩስ በተደረገ ሙዚቃ ድምጿን የሰማነው በሙዚቃዊ ፕሮዲዩስ በተደረገው ' ሻላ' ሙዚቃ ላይ ነው።

በተለያዩ ሀገር አቀፍ መድረኮች ላይ ትሳተፍ እንጂ ሌላው ዙፋን መለያዋ የምትደምቅበት አውድ የብሄር ብሄረሰብ በዓል ነው። ዙፋን ከምትሰራቸው የብሄረሰብ ሙዚቃዎችና ከነርሱም ውጪ የምትወዳቸው ሙዚቃዎች ብዙ ናቸው። ዙፋን በሰራችባቸው የባህል ኪነቶች ውስጥ ሌሎችን በማዝናናት ብዙ ትዝታ ትታለች።  የአሪ ብሄረሰብ መገለጫ ከሆኑት አለባበስና አጌያጊያጥ አንዱ ዚኢ የተባለው የፊት ንቅሳት ይገኝበታል። ዙፋን ታዲያ ብዙ ቦታ የተለያዩ ብሔር ብሄረሰቦችን አልባስና ማጌጫ በመልበስ በቻለችው ልክ ባህሏን ታስተዋውቃለች።

ዙፋን ሙዚቃን በመምረጧ ብዙ ዋጋ ከፍላለች፤ ትልቁ ዋጋ ግን ከቤተሰቦቿ መራራቋ ነበር። ዛሬም ድረስ ለይቅርታ ደጅ መጥናቷን አላቆመችም። አሁንም ይቅርታ አድርጉልኝ ትላለች።

የባህል ሙዚቃና ጭፈራ፤ ማህበራዊ ጥበብን አንድ ስፍራ ላይ ማየት ለወደዱ ከፊታችን ሁለት ልዩ ቀናት አሉ። ከህዳር አጋማሽ እስከ ታህሳስ አንድ የሚዘልቀው የአሪ ብሄረሰብ የዲሽታ ግና የዘመን መለወጫ በዓልና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ኅዳር 29 የሚከበረው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል፡፡

 

በአክሱማዊት ገብረ ሕይወት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ:

ተያያዥ ዜናዎች: