ፈረንሣይ በወታደራዊው መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን የሀገሪቱ ምድር ጦር አዛዥ ጄነራል ፒየር ሺል ገለጸዋል።
በጄነራል ፒየር ሺል የተመራ የፈረንሣይ ወታደራዊ ልዑክ ከኢፌዴሪ መከላከያ አመራሮች ጋር መክሯል።
ምክክሩ የሁለቱን ሐገራት ወታደራዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ሲሆን፤ በቀጣይ በሚኖሩ የሰላም ማስከበር ኦፕሬሽኖች ላይም አጠንጥኗል።
የወታደራዊ ትብብሩ መጠናከር የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ያደረጓቸውን ስምምነቶች ተከትሎ የሚፈጸም እንደሆነም ነው የተመላከተው።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ እየሠራችው ባለው ሥራ መደሰታቸውን የገለጹት ጄነራል ፒየር ሺል፤ በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
አክለውም፥ በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተሳትፎ አስፈላጊ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።
ፈረንሣይ ለጋራ ተጠቃሚነት በወታደራዊ ቁሳቁስ እና በሰው ኃይል ስልጠና ያልተቆራረጠ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ጦር በአፍሪካ ጠንካራ ኃይል መሆኑን የገለጹት የመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄነራል ይመር መኮንን፤ ዘመኑ በሚጠይቀው ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ታግዘን ግዳጅ ለመወጣት ከፈረንሣይ ጋር በትብብር እንሠራለን ብለዋል።
የፈረንሣይ ምድር ጦር አዛዥ ጄነራል ፒየር ሺል በነገው ዕለትም ከኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተገናኝተው እንደሚመክሩና ጉብኝት እንደሚያደርጉ ከመከላከያ ሚዲያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#ebcdotstream #Ethiopia #France #MilitaryCooperation