ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው እና ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር በመሆን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዘርባጃን ባኩ ገብተዋል።
በባኩ ሄዳር አሊዬቭ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተደረገላቸው አቀባበል የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ እና ትርጉም ያለው ደረጃ የሚያሸጋግር የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
ይህ ጉብኝት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጠንካራ ትብብር እየጎለበተ የመጣውን የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጸና እንደሆነ ይታመናል።
የእሳቶች ምድር - አዘርባጃን
አዘርባጃን በታሪክ እና በተፈጥሮ ሀብቷ "የእሳቶች ምድር" (The Land of Fire) በመባል ትታወቃለች።

ይህ ስያሜ የተሰጣት ከመሬቷ በታች ባለው የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ምክንያት ለዘመናት ሳይጠፉ በሚነድዱ "ያናር ዳግ" (የሚነደው ተራራ) መሰል ተፈጥሯዊ እሳቶች ሳቢያ ነው።
ይህ የምድሯ ምስጢራዊ እሳት ለሀገሪቱ ጥንታዊ ማንነት እና ለዘመናዊው የኢነርጂ ኃይሏ ዋነኛ መገለጫ ነው።
የልማት እና የለውጥ ጉዞ
አዘርባጃን በቅርብ ዓመታት በዩራሲያ ቀጣና የኢነርጂ እና የሎጅስቲክስ መዋቅርን በመቀየር ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።
ይህች በቀጣናው በልማት የደመቀች ሀገር ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት እና የዲፕሎማሲ ተሞክሮዎችን እያጋራች ነው። የሀገሪቱ የዘመናዊነት ጉዞ በ"ብሔራዊ መሪዋ" ሄይዳር አሊዬቭ ስትራቴጂያዊ ዕይታ የተጀመረ ሲሆን፣ እኒህ “የአዘርባጃን አባት” የሚባሉት መሪ፣ ሀገሪቱ ከሶቪየት ኅብረት መፈራረስ በኋላ የገጠማትን ቀውስ በብልህነት ተቋቁማ ዛሬ የዓለም የንግድ እና ትራንዚት የስበት ማዕከል እንድትሆን አስችለዋታል።
በ"አዘርባጃኒዝም" እሳቤ ላይ የተገነባው የሀገር ግንባታ ሂደት፣ በአሁኑ ወቅት ሰፊ መዋቅራዊ ለውጥ እያካሄደች ላለችው ኢትዮጵያ ትልቅ ስልታዊ ትምህርት የሚገኝበት ነው።
ከአሳን (ASAN) እስከ መሶብ (MESOB)
ሁለቱ ሀገራት በተለይም በሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የጀመሩት ትብብር ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ይገኛል።
አዘርባጃን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማነቱ የተረጋገጠውን የ"አሳን" (ASAN) የአገልግሎት ሞዴል ለኢትዮጵያ አጋርታለች።

ኢትዮጵያም በዚህ ተሞክሮ ላይ በመመሥረት የ"መሶብ" (MESOB) የተቀናጀ የአገልግሎት ማዕከልን አቋቁማ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ እያስመዘገበች ነው።
መሶብ በርካታ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ሥር በዲጂታል መንገድ ተደራሽ በማድረግ፣ ቢሮክራሲን እና ሙስናን በመቀነስ የዜጎችን እንግልት በማቃለል ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ነው።
የአየር ንብረት እና የመልሶ ግንባታ ተሞክሮ
ሀገራቱ የአየር ንብረት ፋይናንስ ለአዳጊ ሀገራት እንዲቀርብ በጋራ እየሠሩ ሲሆን፣ አዘርባጃን በጉባኤው ዝግጅት ወቅት ያገኘችውን ድርጅታዊ ብቃት እና የቴክኒክ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ቃል ገብታለች።
በተጨማሪም ከግጭት በኋላ በካራባክ ግዛቶች ውጤታማ የሆነችበትን የመልሶ ግንባታ (Great Return) ሞዴል፣ ኢኮኖሚን፣ ደኅንነትን እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማቀናጀት ረገድ ለኢትዮጵያ ሰፊ ተሞክሮ የሚያካፍል ነው።
የንግድ እና የኢኮኖሚ ትስስር
በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍም የኢትዮጵያ ቡና እና ቅመማ ቅመም ወደ አዘርባጃን የሚላኩበት ዕድል እየሰፋ ሲሆን፣ በምላሹም የኢንዱስትሪ ማሽነሪዎችን እና የነዳጅ ውጤቶችን ከአዘርባጃን ለማስገባት ሰፊ ውይይቶች እየተደረጉ ይገኛሉ።
ይህ በትብብር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተው ግንኙነት፣ ኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ሉዓላዊነቷን በማጠናከር እና ዘመናዊ ተቋማትን በመገንባት በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተፅዕኖ ለማሳደግ የምታደርገውን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፋል።
በለሚ ታደሰ