የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተደድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ርዕሰ መስተደድር አሻድሊ ሀሰን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ርዕሰ መስተደድር አሻድሊ እና አምባሳደር ሂሮኖሪ በሁለትዮሽ የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
አቶ አሻድሊ በዚሁ ወቅት፥ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለው የመልማት አቅም የሕብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉ ከጎረቤት ሀገራት በርካታ ስደተኞችን በመቀበል እያስተናገደ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህ ስደተኞች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በሰላም እየኖሩ ነው ብለዋል።
የኅብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተደድሩ፤ በክልሉ ያለውን የሆስፒታሎች ቁጥር እና አቅም ለማሳደግ በዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች መደገፍ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በክልሉ ርዕሰ መዲና አሶሳም አበረታች የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በከተማዋ ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

አምባሳደር ሂሮኖሪ በበኩላቸው፥ የክልሉ መንግሥት ላደረገላቸው አቀባበል አመስግነው፤ የአሶሳ ሆስፒታልን የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ትምህርት ቤቶችን እና የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በአሶሳ ሆስፒታል በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ የማስፋፊያ ሕንፃዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ክትትል እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጄንሲ (JICA) በጤና፣ በትምህርት እና በንፁህ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኤጀንሲው ከክልሉ ጋር የሚያደርገውን የማኅበረሰብ ልማት ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በነስረዲን ሐሚድ
#ebcdotstream #Ethiopia #Japan #Development #Cooperation