ኢትዮጵያ ወጤታማ ተሳትፎ ያደረገችበት እና በአንጎላ ዋና ከተማ ሉዋንዳ ለሁለት ቀናት የተካሄደው 7ኛው የአፍሪካ ኅብረት እና የአውሮፓ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የጋራ መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ።
በአንጎላ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሎሬንሶ እና በአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ በጋራ ሊቀመንበርነት የተመራው ጉባዔ የህብረቶቹ የአጋርነት ምስረታ 25ኛ ዓመት የተከበረበትም ነበር።
ሁለቱ አህጉራት በጉባዔው ማጠናቀቂያ ባፀደቁት የጋራ መግለጫ፥ ለ2030 የጋራ ራዕይ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፣ አጋርነቱ በፖለቲካ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት እየተጠናከረ መምጣቱን አድንቀዋል።
የጋራ መግለጫው ቃል ኪዳኖች በሰላም እና ዓለም አቀፍ ትብብር ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፤ በዩክሬን፣ በፍልስጤም አስተዳደር፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በሌሎችም ሀገራት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የማያወላውል ድጋፍ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
በተለይ በሱዳን ያለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው፤ በአፍሪካ ህብረትና በኢጋድ አመቻቺነት በሱዳን ዜጎች ባለቤትነት የሚመራ ወደ ወጥ እና ሲቪል ሽግግር የሚያመራ የፖለቲካ ሂደት እውን እንዲሆን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

በኢኮኖሚው ዘርፍም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ትግበራን ለማፋጠን የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል። የአፍሪካ-አውሮፓ ኢንቨስትመንት ፓኬጅ ትግበራ ላይ ጉልህ መሻሻል መኖሩም ተነስቷል።
ዓለም አቀፍ የዕዳ አስተዳደር ይበልጥ ግልጽ፣ ውጤታማ እና ሊተነበይ የሚችል የዕዳ አስተዳደር ዘዴን እንዲከተል ጥሪ አቅርበዋል።
በስትራቴጂያዊ ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ፣ ሁለቱ ኅብረቶች በአፍሪካ-አውሮፓ አረንጓዴ ኃይል ኢኒሼቲቭ በኩል እስከ 2030 ድረስ በአፍሪካ ቢያንስ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ከካርቦን ነፃ የሆነ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ፣ ሁለቱ ወገኖች የፓሪሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር የገቡትን ቃል አድሰው፣ የአየር ንብረት ፋይናንስን በተመለከተ እስከ 2035 ድረስ በየዓመቱ ቢያንስ 1.3 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማሰባሰብ በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የጤናው ዘርፍ ዓለም አቀፍ አሠራር እንዲሻሻል አጥብቀው ጠይቀው፣ በተለይም የወረርሽኝ መከላከልና ምላሽን እንዲሁም የአፍሪካን የጤና አገልግሎት ግብዓቶችን የማምረት ጥረትን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።
በፍልሰት ዙሪያም በጋራ ኃላፊነት ላይ የተመሠረተ ትብብርን መነሻ በማድረግ በሕገወጥ ስደት እና የሰው ዝውውርበን እንዲሁም በግዳጅ የመፈናቀል መሠረታዊ መንስዔዎች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በአፍሪካ ኅብረትና በአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስብሰባ ላይ የሚፀድቅ የትብብር ዕቅድ ላይ በቀጣይ ስድስት ወራት በጋራ ለመሥራት ተስማምተው ለ8ኛው ጉባዔ ደግሞ በብራስልስ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።
በሙሐመድ አልቃድር
#ebcdotstream #Luanda #7thAU-EUSummit