Search

ሪያል ማድሪድ ከ ባርሴሎና ተጠባቂው የዋንጫ ጨዋታ

እሑድ ጥር 03, 2018 56

በስፔን ሱፐር ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ በኤል ክላሲኮ የምንጊዜም ተቀናቃኞቹ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ከ2020 ጀምሮ በአዲስ የጨዋታ ቅርጽ እየተካሄደ የሚገኘው የስፔን ሱፐር ካፕ በዚህ ዓመት ለ42ኛ ጊዜ ይደረጋል፡፡
ባርሴሎናን ከ ሪያል ማድሪድ ያገናኘው ተጠባቂው የዋንጫ ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሳዑዲ አረቢያ በንጉስ አብደላ ስፖርት ስታዲየም ይደረጋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት አራት ቡድኖች ብቻ እየተሳተፉበት በሚገኘው የስፔን ሱፐር ካፕ ባርሴሎና አትሌቲክ ቢለባኦን 5 ለ 0 በማሸነፍ ነው ለዛሬው የዋንጫ ጨዋታ የደረሰው፡፡ በሌላ በኩል ሪያል ማድሪድ የከተማ ተቀናቃኙን አትሌቲኮ ማድሪድ 2 ለ 1 በማሸነፍ ነው ለፍጻሜ መድረስ የቻለው፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ለ3ኛ ተከታታይ ጊዜ በተገናኙበት ፍጻሜ የሪያል ማድሪዱ አለቃ ዣቢ አሎንሶ በክለቡ የመጀመርያ ዋንጫውን ለማሳካት፣ የባርሴሎናው አሰልጣኝ ሀንሲ ፍሊክ ደግሞ በተከታታይ አሸናፊ ለመሆን እንደሚፋለሙ ይጠበቃል፡፡
ለ262ኛ ጊዜ በሚደረገው ኤል ክላሲኮ አንድሬ ቴርስቴገን፣ ጋቪ እና ክርስቲያንሰን ከባርሴሎና በኩል በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሲሆኑ ላሚን ያማል ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል፡፡
ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ እና ኤደር ሚሊታኦ በማድሪድ በኩል ከስብስቡ ውጭ ሲሆኑ ሮድሪጎ፣ አንቶኒዮ ሩዲገር እና ራውል አሴንሲዮ ሊሰለፉ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ባለፈው ዓመት በተገናኙበት ፍጻሜ ባርሴሎና 5 ለ 2 በማሸነፍ የስፔን ሱፐር ካፕን ለ15ኛ ጊዜ ማሳካቱ ይታወሳል፡፡
 
በአንተነህ ሲሳይ
All reactions:
1.4K