የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር ተወያይተዋል።
ዶክተር ጌዲዮን በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ጠንካራ እና በሁኔታዎች የማይቀየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት አንሥተዋል።
የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የረዥም ጊዜ ወዳጅነት፣ ትብብር እና በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸው፣ ቻይና ለኢትዮጵያ ልማት እያደረገችው ያለውን ድጋፍ በማድነቅ ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ቻይና ያቀረበችውን የአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና ልማት ኢኒሼቲቭ ተነሣሽነት ትኩረት በመስጠት በቀጣናው ያሉ የደኅንነት፣ ልማት እና አስተዳደር ተግዳሮቶችን ለመፍታት ያለውን ጠቀሜታ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የኢትዮ-ቻይና አጋርነትን በተለያዩ ባለብዙ መድረኮች ማለትም በአንድ ቀበቶ እና መንገድ (Belt & Road) ኢኒሼቲቭ፣ በቻይና-አፍሪካ ትብብር መድረክ፣ ብሪክስ-ፕላስ እና በተባበሩት መንግሥታት ማዕቀፎች ጨምሮ በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው፣ ወደ አፍሪካ ያደረጉት ጉብኝት በጎርጎሮሳውያኑ 2026 የመጀመሪያው ወደ ውጭ ያደረጉት ጉዟቸው መሆኑን እና ኢትዮጵያ የመጀመሪያ መድረሻቸው መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ዘላቂ አጋርነት እና ኢትዮጵያ ደግሞ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኗን ገልጸዋል።
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም ዓይነት አጋርነት በተለያዩ የትብብር ዘርፎች የበለጠ ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የግንኙነት መድረኮች ላይ ስትራቴጂካዊ ቅንጅትን ለማጠናከር መስማማታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።