አራዳ ሌግዠሪ ሞል በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆነው የቤት ዕቃዎች አምራች አሽሊ ፈርኒቸር ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱ ኩባንያው በሞሉ ውስጥ የምርት ማሳያና መሸጫ እንዲከፍት የሚያስችል ነው ተብሏል።
አሽሊ ፈርኒቸር በዓለም ዙሪያ ከ1 ሺህ በላይ ቅርንጫፎችና ከ35 ሺህ በላይ ሠራተኞች ያሉት ግዙፍ አምራች ድርጅት ነው።
ይህ ስምምነት ዓለም አቀፍ ብራንዶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ ዕድል ከመፍጠሩ ባለፈ፣ ለሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ በግዙፍነቱና በዘመናዊነቲ ቀዳሚው እንደሚሆን የሚጠበቀው ፣ በአሁኑ ወቅት በፒያሳ ዐድዋ ሙዚየም ፊት ለፊት በግንባታ ላይ የሚገኘው አራዳ ሞል በ16 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፤ አጠቃላይ የፎቅ ስፋቱ 115 ሺህ ካሬ ሜትር መሆኑ ተጠቅሷል።
የግንባታ ሂደቱ እስካሁን ለ1 ሺህ 200 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተመላክቷል።
የሕንጻው 48 በመቶ ለውጭ ሀገር ካምፓኒዎች የሚውል ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ ለሀገር ውስጥ ድርጅቶች በኪራይ ይተላለፋል ተብሏል።
ሞሉ በውስጡ ሱፐር ማርኬቶችን፣ የፋሽን መሸጫዎችን፣ ሲኒማ፣ ጂምናዚየም፣ ባንኮችን፣ የሕክምና ክሊኒኮችንና ምግብ ቤቶችን ጨምሮ ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶችን እንደሚይዝ ታውቋል።
ዓለም አቀፍ ብራንዶች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ ምቹ ዕድል መፍጠሩን እና ዓለም አቀፉ አሽሊ ፈርኒቸር በኢትዮጵያ ገበያ መግባቱ ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።
በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ የአሜሪካው አምባሳደር አርቪን ማሲንጋ ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝቷል።
በአንዋር አህመድ