የቻይና የሳይበር ተቆጣጣሪ አካል፥ የሰው ልጅን ባሕርይ ተላብሰው የተነደፉ እና ከተጠቃሚዎች ጋር የስሜት መስተጋብር የሚፈጥሩ የአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ (AI) አገልግሎቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ ያዘጋጀውን ረቂቅ ሕግ ለሕዝብ አስተያየት አቅርቧል።
ቻይና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ዓለምን ለመምራት በሚደረገው ውድድር ከግንባር ቀደሞቹ መካከል ናት።
በሌላ መልኩ ሀገሪቱ የአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ ፈጣን ዕድገት ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ስጋት ለመቀነስም እየሠራች ትገኛለች።
የቻይና የሳይበር ተቆጣጣሪ አካል ያወጣው ረቂቅ ሕግም ይህንኑ የሚያጠናክር ሲሆን፤ ረቂቅ ሕጉ የተጠቃሚዎችን ደኅንነት የሚጠብቅ እና የአጠቃቀም ሥነ-ምግባርን የሚያጠናክር መሆኑ ተገልጿል።
ረቂቅ ሕጉ ቻይና ውስጥ ለሕዝብ የሚሰጡ የሰው ልጅ ባሕርይን፣ አስተሳሰብን እና የተግባቦት ዘይቤዎችን የተላበሱ እና በጽሑፍ፣ በፎቶ፣ በድምፅ፣ በቪዲዮ እና በሌሎች አማራጮች ተዘጋጅተው ከሰው ልጅ ጋር ስሜታዊ መስተጋብር በሚፈጥሩ የኤአይ ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል።
የአገልግሎት አቅራቢዎች የተጠቃዊዎች የኤአይ ምርትን ወይም አገልግሎትን የመጠቀም ዝንባሌ ከመጠን አልፎ ወደ ሱስ ደረጃ ስለመድረሱ ምልክት ሲያዩ ጣልቃ እንዲገቡ ረቂቅ ሕጉ ያስገድዳል።
እዲሁም የአገልግሎት አቅራቢዎች በምርት ዑደቱ የደኅንነት ኃላፊነቶችን መውሰድ እንዲሁም የአልጎሪዝም ግምገማ፣ የዳታ ደኅንነት እና የግል መረጃ ጥበቃ ሥርዓቶችን ማቋቋም ይጠበቅባቸዋል።
ረቂቁ ሊከሰቱ ለሚችሉ የሥነ-ልቦና አደጋዎችም ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣ የኤአይ ምርት ወይም አገልግሎት አቅራቢዎች የተጠቃሚዎችን ሁኔታ ለይተው እንዲያውቁ እና የተጠቃሚዎችን ስሜት እና በአገልግሎቱ ላይ ያላቸውን የጥገኛነት ደረጃ እንዲገመግሙ ይጠበቅባቸዋል።
ተጠቃሚዎች ከፍተኛ ስሜቶች ወይም የሱሰኝነት ባሕርይ እንዳዳበሩ ከተረጋገጠ አቅራቢዎች ጣልቃ በመግባት አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባቸው በረቂቁ መብራራቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
የኤአይ አገልግሎቶች ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ አሉባልታን የሚያሰራጩ፣ ዓመፅን ወይም ፀያፍ ድርጊትን የሚያበረታቱ ይዘቶችን ማመንጨት የለባቸውም ሲልም ረቂቅ ሕጉ ቀይ መስመር አስምሯል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream #AI #China #AIregulation