የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሀገራት የብልፅግና እና የሉዓላዊነት ቁልፍ በቴክኖሎጂ አቅም ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን የተገነዘበችው ኢትዮጵያ፤ ከዚህ ቀደም ጥቂት በልፅገዋል የሚባሉ ሀገራት ብቻ በበላይነት ይዘውት የነበረውን የቴክኖሎጂ ዘርፍ በመቀላቀል ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ከነደፋቸው ስትራቴጂካዊ ትልሞች መካከል ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለዘርፉ የተሰጠውን ትልቅ ትኩረት ያሳያል ይላሉ የዘርፍ ባለሙያዎች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለ ቴክኖሎጂ በተለይም ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) አስፈላጊነት ሲያነሱ፤ ዘርፉ ለኢትዮጵያ የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን የልማት እና የብልፅግና ጉዟችንን ለማፋጠን ወሳኝ የለውጥ መሣሪያ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህም አትችልም በሚል የተዛባ ትርክት ውስጥ የነበረችውን ኢትዮጵያ፤ ዛሬ ያንን ትርክት በመቀየር አቅም አለኝ ወደሚል የመሪነት መንፈስ እንድትሸጋገር በማድረግ ላይ ይገኛል።
በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ (STEM) እንዲሁም በሥራ ፈጠራ የአቅም ግንባታ ላይ የሚሠራው የስቴም ፓወር የኢትዮጵያ ኃላፊ ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) ከኢቲቪ “አዲስ ቀን” መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶች ለቴክኖሎጂ አብዮት መቀጣጠል ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም፣ የሀገር ውስጥ ኢኖቬሽንን በማበረታታትና ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በመደገፍ ሰፊ ውጤት እያገኘች መሆኑን ጠቁመዋል።
በርካታ ባለሙያዎች ከውጭ ሀገራት ጋር በመሥራት የሶፍትዌር እና የሃርድዌር ሽያጭ በማከናወን፤ ለራሳቸው ገቢ ለሀገራቸውም የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መቻላቸውን ኃላፊው የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በማስረጃ አስረድተዋል።
ለወጣቱ የፈጠራ ምቹ ምኅዳር ከመፍጠር አንጻርም የስታርት አፕ አዋጁ ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑንና የተገነቡ መሠረተ ልማቶችም ለቴክኖሎጂው እንቅስቃሴ ጉልበት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ትኩረቱን በስታርት አፕ ሥራዎች ላይ ያደረገው የአይ ኮኔክት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ፊሊጶስ ወንድወሰን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የጀመረችው እንቅስቃሴ ለወጣቱ በርካታ የሥራ ዕድሎችን ይዞ እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት ባለፉት አምስት ዓመታት ተቋማትን ከመገንባት ጀምሮ ሰፊ ሥራዎችን ስታከናውን መቆየቷንም በበጎ ጎን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ የቀጣይ አምስት ዓመታት መሪ ዕቅድ የሆነውን “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂን ይፋ ማድረጓን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፤ ስትራቴጂው ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረውና የሀገሪቱን የዲጂታል ምጣኔ ሀብት እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት