ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ባወጡት የጋራ የሚኒስትሮች መግለጫ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ወቅት በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ ውይይት ማድረጋቸውን የጋራ መግለጫው አመላክቷል።
የጋራ ውይይቱ በቀጣናው እና በሌሎች አካባቢዎች የሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ የታዩ ዋና ዋና ለውጦችን ለመገምገም ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ሁለቱም ወገኖች መረጋጋትን ለማስፈን እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ላላቸው የጋራ ቁርጠኝነት አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሁለቱም ወገኖች የቆየውን ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸውን ጥልቀት እንዲሁም በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች እና በኢትዮጵያ ግንኙነት ውስጥ የሚታየውን የጋራ መከባበር እና የትብብር ጠንካራ መሠረት በድጋሚ ማረጋገጣቸውም በመግለጫው ተጠቁሟል።
ሁለቱ ሀገራት በሰላም እና ደኅንነት፣ በግዛት አንድነት እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በማስፋፋት እና ችግሮችን በመከላከል ረገድ ያላቸውን አጠቃላይ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ኢትዮጵያ የኮፕ32 አዘጋጅ መሆኗን በደስታ መቀበሏን ጠቁማ፣ ሁለቱም ወገኖች በ198 ሀገራት የተደረሰውን የታሪካዊውን "የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ስምምነት" (UAE Consensus) እና የኮፕ28 ውጤቶችን መሠረት በማድረግ የኮፕ32 የአየር ንብረት አጀንዳን ለማራመድ መስማማታቸውም ተመላክቷል።
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ስኬታማ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ያተኮረ ውጤት እንዲመዘገብ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ሁለቱ ሀገራት የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ማውገዛቸውን በጋራ መግለጫቸው አስታውቀዋል።
የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች እና ለሰብዓዊ ረዳት ሠራተኞች ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ሁለቱ ወገኖች የእርስ በርስ ጦርነቱን የማቆም ቀዳሚ ኃላፊነት የተፋላሚ ወገኖች መሆኑን አስምረውበታል።
ኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሰላምን ለማስፈን፣ ቀጣናዊ መረጋጋትን የሚፈታተኑ ችግሮችን ለመፍታትም ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ከቀጣናዊ የደኅንነት ጉዳዮች በተጨማሪ ሁለቱም ወገኖች በዓለም አቀፍ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውም ባወጡት የጋራ መግለጫ አመላክተዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም