ባሕረ-ገብ የሆነው የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በተጠንቀቅ የሚጤንበት የምድር ወሳኝ ክፍል ነው። በዚህ ቀጠና የጦር ሰፈር ለመመሥረትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ ኃያላን ሀገራት በሺዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው መጥተዋል።
አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይና ጃፓን በቀጠናው የጦር ሰፈር ከመሠረቱ ሀገራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ሀገራቱ ይህን ሁሉ ርቀት አቋርጠው በስፍራው የተገኙት ለሉዓላዊነታቸው መከበርና ለብሔራዊ ጥቅማቸው መጠበቅ ሲሉ ነው።
የዓለም አቀፍ ንግድ የደም ቧንቧ ተደርጎ ከሚመሰለው ቀይ ባሕር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ በተጠነሰሰባት ሴራ አማካኝነት የባሕር በር እንዳይኖራት ተደርጓል።
በበርካታ ምክንያቶች ከባሕሩ እንድትርቅ የተደረገችው ኢትዮጵያ፣ እንደ ሀገር ለመቀጠል የባሕር በር ባለቤት ለመሆን የሚያስችሉ አማራጮችን መፈለግና ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደኅንነት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።
የባሕር በር አልባነት ለኢኮኖሚ መላሸቅና ለሕልውና መናጋት የሚያስከትለውን ችግር በአግባቡ ማጤን እንደሚገባ የገለጹት ተመራማሪው፤ የትውልዱ ጥያቄ የሆነው የባሕር በር ጉዳይ ከሸቀጥ ማመላለሻነት የዘለለ ትርጉም ያለው መሆኑን ልብ ሊባል እንደሚገባ በኢቲቪ ዳጉ መሰናዶ ላይ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የእራሷ የባሕር በር እንዲኖራት ያስገድዳታል ያሉት ተመራማሪው፤ ይህ አጀንዳ የአንድ ፓርቲ አቋም ብቻ ሳይሆን፣ የየትኛውም አስተዳደርና የመላው ሕዝብ የጋራ አቋም ሆኖ እንዲቀጥል መሥራት ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ።
የባሕር በርን ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር ሀገራዊ አንድነት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በዚህ አጀንዳ ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሚሆንም አመላክተዋል።
በአፎሚያ ክበበው