የሃላባ የዘመን መለወጫ "ሴራ" በዓል በባህላዊ የዘመን አቆጣጠር ስርዓት የማህበረሰቡ ሀገር በቀል እውቀት ማሳያ ሲሆን በየዓመቱ ከታህሳስ መጨረሻ እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ባሉ ቀናት ውስጥ ይከበራል።
በሃላባ ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠር ቀመር "መንገሳ" የዓመቱ የመጨረሻው ወር ሲሆን ይህ ወር የአሮጌው ዓመት ማብቂያ እና ወደ አዲሱ ዓመት መሽጋገሪያ ነው ።
የአካባቢው ተወላጆች በዚህ ወር አዲሱን ዓመት ለመቀበል አርሶ አደሩ በእርሻው፤ ነጋዴው በንግዱ ሁሉም በየተሠማራባት መስክ ለአዲስ ስኬት እራሳቸውን በስነ- ልቦና የሚያዘጋጁበት ወር ነው።
የሴራ በዓል በውስጡ በርካታ እሴቶችን ይዟል። በየዓመቱ በበዓሉ መዳረሻ እድሜያቸው የደረስ ታዳጊዎች ግርዛት በመፈፀም ወደ ወጣትነት የሚሻገሩበት እና ሃላፊነት የሚቀበሉበት ሥርዓት ይፈፅማሉ፡፡
በበዓሉ ወቅት አባቶች የተጣሉ ሰዎችን በማስታረቅ በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ የሚያደርጉበት ማህበራዊ ሃላፊነት ከበዓሉ መገለጫዎች መካከል ይገኛል።
የዘንድሮው የሃላባ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ "የሴራ" በዓል ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መንገድ በሃላባ ቁልቶ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
የሃላባ "ሴራ" ማህበረሰቡ በዘመናት ሂደት ያጎለበታቸው የእለት ተእለት የሕይወት መስተጋብር የሚመራበት ባህላዊ አስተዳደር ስርዓት ነው።
"ሴራ" ወይም (የባህላዊ የአስተዳደር ሕግ) በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ በባህላዊ ፍልስፍናው የተለያዩ ጉዳዮችን የሚመራበትን ስርዓት አበጅቷል።
“ኦገቴ ሴራ” የተሰኘ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት እና “ሚሻላ ሴራ” በመባል የሚታወቀው የተመረዳዳትና የመደጋገፍ ሥነ-ስርዓቶችም ተጠቃሽ የአካባቢው ባህሎች ናቸው፡፡
እነዚህ ባህላዊ ሕጎች ዘመናትን ተሻግረው ዛሬ ላይ የደረሱት በቃል እና በተግባር በመኖር በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠብቀው ነው።
በሚካኤል ገዙ