ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያዎች ትልቅ ለውጥ እያስተናገዱ ነው። በአውሮፓውያኑ 2025 ከተከሰቱት ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ ታሪኮች መካከል አንዱ፣ መገናኛ ብዙኃን ብዙም ትኩረት ያልሰጡት የብሪክስ አዲስ የክፍያ ሥርዓት ማስጀመር ነው።
የብሪክስ ጥምረት በዓለም ዙሪያ ያሉ 185 ሀገራት በቻይና ገንዘብ ሬንሚንቢ (RMB) የንግድ ልውውጥ እንዲያካሂዱ የሚያስችል አዲስ የክፍያ ሥርዓት በተሳካ ሁኔታ አስጀምሯል።
ይህ ሥርዓት ከአፍሪካ፣ ከደቡብ አሜሪካ እና ከእስያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት አዲስ አማራጭ እና ፖለቲካዊ ከሚመስሉ ጫናዎች እንዲያመልጡ ያስችላልም ተብሏል።
የቻይና ሬንሚንቢ አሁን በአሜሪካን ዶላር በመቀጠል በዓለም አቀፍ የንግድ ፋይናንስ ውስጥ ሁለተኛው በስፋት ጥቅም ላይ የዋለ ገንዘብ ሆኗል፤ ድርሻውም ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ወደ 7.6 በመቶ አድጓል።
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የቻይና ባንኮች ለውጭ ሀገራት የሰጡት የሬንሚንቢ ብድሮች አራት እጥፍ ጨምረዋል። ለምሳሌ፣ ኢንዶኔዢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዩዋን ቦንድ ስትሸጥ፣ ባለሀብቶች ከጠበቀችው መጠን ሦስት እጥፍ ያህል ፍላጎት አሳይተዋል።
በርካታ ታዳጊ ሀገራት ብድራቸውን ከአሜሪካ ዶላር ወደ ቻይና ሬንሚንቢ በመቀየር ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
የብሉምበርግ ትንበያዎች እንደሚጠቁሙት በአውሮፓውያኑ 2050 የቡድን 7 ሀገራት የዓለምን ጠቅላላ ምርት (GDP) የሚቆጣጠሩት 18% ብቻ ሲሆን፣ የብሪክስ አባላት ደግሞ 50% የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ።
ይህ መረጃ የዓለም የኢኮኖሚ ኃይል ወደ ምሥራቅና ደቡብ እየተቀየረ መሆኑን የሚያመላክት አንድ ማስረጃ ሆኖ እየተነገረ ነው።
ቻይና ከ53 የአፍሪካ ሀገራት ጋር የዜሮ ታሪፍ የንግድ ስምምነት መፈረሟ እና የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሀገራት ማኅበር (ASEAN) ከቻይና ጋር ያላቸውን የንግድ ስምምነት ማጠናከሩ፣ ቻይና በአብዛኛው ዓለም ቁልፍ የንግድ እና የፋይናንስ አጋር እየሆነች መምጣቷን ያረጋግጣል ተብሏል።
በሰለሞን ገዳ