Search

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጣቸው

ዓርብ ኅዳር 19, 2018 8

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እና ረዥም ዓመት አገልግለው በጡረታ ለተሰናበቱ ሠራተኞች የእውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የ3ኛው ዙር ለታክስ ሕጎች ተገዢ ሆነው ግብራቸውን ለከፈሉ 79 ግብር ከፋዮች እውቅ እና ሽልማት ሰጥቷል፡፡
ከነዚህ ውስጥ 10 ግብር ከፋዮች ደግሞ በክልሉ ሁሉም ቦታዎች ያለቅድመ ሁኔታ ማንኛውንም አገልግሎት በቅድሚያ እንዲያገኙ ልዩ መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የክልሉ ገቢ አፈጻጸም በየዓመቱ ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
ለዚሁም ስኬት በክልሉ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ የግል ባለሀብቶች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ይህንኑን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በየደረጃው ተገቢው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች በክልሉ ያሉ እምቅ የመልማት አቅሞችን በተገቢው ለመጠቀም ባለሀብቶች በዘርፉ በሥፋት እንዲሰማሩ አመላክተዋል።
በከተሞች የሚስተዋለውን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ከሊዝ ነጻ መሬት እንደሚያቀርብ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጋር ተባብረው በሪል ስቴት ዘርፍ እንዲሰማሩ ጠይቀዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በበኩላቸው፤ በክልሉ 60 በመቶ የመንግሥትን ወጪ በገቢ ለመሸፈን መቻሉን ጠቅሰዋል።
ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በታማኝነት እንዲከፍሉ በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።
በሰለሞን ባረና