ኢትዮጵያ የታሪክ ሀብታም ከሆኑ ሀገራት መካከል ስሟ ቀድሞ ይጠቀሳል፡፡ ሀገሪቱ ካሏት ግዙፍ ታሪኮች መካከል ደግሞ የረጅም ዘመን የመንግሥትነት ሥርዓት አንዱ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያላት የሥርዓተ መንግሥት ታሪክ ግን በዕድሜው ልክ ጠንካራ እና ወጥነት ያለው ሳይሆን በመንግሥታት መለዋወጥ ውስጥ ውጣውረድ የበዛበት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ለዚህ ደግሞ አንዱ ምክንያት እየደመሰሱ የመቅዳት አባዜ ሲሆን ኢትዮጵያን ካስተዳደሩ መንግሥታት መካከል ጥሎ ያልወድቀን ማግኝቱ ከባድ ነውና ከውጣውረዶቹ አንዱ ሆኖ ይነሳል፡፡
እንዲህ ያለው ውጣውረድ ደግሞ አትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ የተቋማት ግንባታ እንዳይኖራት ያደረገ ክስተት ሆኗል፡፡
እነዚህ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው የመንግሥታት ለውጥ የማያውካቸው ይልቁንም ለመንግስት አቅም የሚሆኑ እንዲሆኑ ይጠበቃል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ይህን የማረጋገጥ ስራ በብዙ መልኩ ፈተና የበዛበት እንደሆነ ቆይቷል፡፡
የነበረውን የማፍረስ ችግር ጎልቶ የሚታየው አንዱ ሥርዓት ሄዶ ሌላው ሥርዓት ሲተካ መሆኑ ተቋማት በመንግስታት ለውጥ ውስጥ እየተጠናከሩ እንዳይሄዱ ትልቅ ምክንያት ሆኗል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከተመሰረተችበት የረጅም ዘመን ጉዞ አብላጫው የጦርነት መሆኑ በተቋማት ግንባታ ውስጥ የሁልጊዜ እንቅፋት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ጥንታዊ የመንግሥት ስርዓት ባለቤት ብትሆንም የነበረውን የማፍረስ ችግር ፖለቲካዋ ኋላቀር ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል፡፡
መንግሥታዊ ተቋማት መሠረታቸው ጠንካራ ካልሆኑ የግለሰቦች ተክለ ሰብዕና ብቻ ገዝፎ ለዘላቂ የሀገረ መንግስት ግንባታ የሚሰጠው ትኩረትም ሆነ ቁርጠኝነት እዚህ ግባ የማይባል ይሆናል፡፡
በኢትዮጵያም ይህ ችግር በመኖሩ የአገር ግንባታ ሒደቱ ላይ ስምምነቶች እንዳይኖር አድርጎት ቆይቷል።
የሰዎች በነፃነት መንቀሳቀስ እና መኖር የሚረጋገጠው ሕግ አስከባሪ ተቋማት በጠንካራ መሰረት ላይ ሲገነቡ ነው፡፡ ዜጎች መብታቸው የሆነውን አገልግሎትን በሥርዓት ማግኘት የሚችሉትም ተቋማቱ ሕግ አክብረው የሚሠሩበት ተቋማዊ ልዕልና ሲኖራቸው ነው፡፡
ተሿሚዎች በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን በአግባቡ ሊሠሩበት የሚችሉት ተቋማቱ ከሕግ ውጪ ዝንፍ እንዳይሉ ከአቅም ጋር እኩል የሚጓዝ ተጠያቂነት ሲሰፍን መሆኑ ግልጽ ነው።
የመንግሥት አሠራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዲኖርው ለተቋማት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት ይገባል፡፡ በአንጻሩ ደካማ የተቋማት ግንባታ በሥልጣን መባለግ፣ ዝርፊያ እና ሥርዓተ አልበኝነት ጉለብት እንዲያገኙ እድል ይሰጣል።
ኢትዮጵያ ውሰጥም እንዲህ ያሉ ችግሮች አጋጥምው ዜጎችም ለፈተና ተጋልጠው ያወቃሉ፡፡
ለዚህ ምክንያት ሆኖ የሚጠቅሰው ኢትዮጵያ ከሥርዓት ወደ ሥርዓት ስትሸጋገር የገጠሟት ችግሮች ይፈቱ የነበረው በጠንካራ ተቋማት እና በሕግ ሳይሆን በግለሰቦችና ቡድኖች ፈቃደኝነት በተዳከሙ ተቋማት ውስጥ ተሆኖ ነው፡፡
እምነት የሚጣልባቸው እና ቅንነት ያለው ጠንካራ ተቋማት ሲገነቡ ፖለቲካዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ የሚያስተካክሉት ድህነት የመቀነስ ሂደቱንም ቀላል ያደርጋሉ፡፡
ጠንካራ ተቋማትን የገነቡ አገራት መሪዎች አገርን በሥርዓት ሲመሩ፣ ሥልጣናቸው ግልጽነትና ተጠያቂነትን ሲያስቀድሙ ይስተዋላል፡፡ ከአንድ ሥርዓት ወደ ሌላ ሥርዓት ሲሸጋገሩም የሚመሩት በሕግ ብቻ ነው፡፡
የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ ኖርዌይ፣ አይስላንድ፣ ስዊድን፣ ኒውዝላንድ እና ዴንማርክን በጠንካራ ተቋሞቻቸው ተጠያቂነትን ያረጋገጡ እና የዳበረ የዴሞክራሲ ባለቤቶች ናቸው ይላቸዋል።
በእነዚህ ሀገራት ዜጎች በመንግስታቸው ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላቸውም መረጃው ይጠቅሳል። የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ደረጃ ከእነዚህ ሀገራት በጣም የራቀ ነው።
ለዚህ ምክንያት ሆኖ የተጠቀሰው ደግሞ አሜሪካውያን በመንግስታቸው ላይ ያላቸው እምነት ዝቅ እያለ በመምጣቱ ነው ይላል የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ።
በተቋማት ግንባታ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡት ታዳጊ ሀገራት ናቸው። ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር እና የፍትህ እጦት ለሚባሉ የሥርዓት በሽታዎችም ተጋላጭ ሆነው ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያም ታዳጊ አገራት የሚፈተኑበት ችግር ችግሯ ነው። ጠንካራና እምነት የሚጣልባቸው ተቋማት የመገንባት ስራዋም የመንግስት ምስረታ ታሪኳን የሚመጥን ባለመሆኑ ገና ብዙ መስራት እንደሚገባት ግልጽ ነው።
ፖለቲካውን ከኋላቀርነት ነፃ ለማውጣት እንዲሁም ድህነትን ለማሸነፍ የሚደረገው ጥረት አቅምን የሚፈትን ነው። መንግሥት ለዚህ ትልቁ ምክንያት ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ጠንካራ ተቋማት ባለመገንባታቸው እንደሆነ ተደጋግሞ ሲነገር ይስተዋላል።
ተቋማት ነፃና ገለልተኛ ሲሆኑ ታማኝነት እና ህጋዊነት መለያቸው ይሆናል። ዜጎችም በመንግሥትና በሚያገለግሏቸው ተቋማት ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ ይሆናል። ይህ ደግሞ ችግሮች ሁሉ በተቋማት ይፈቱልኛል ብሎ የሚያምን ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል። የዚህ ውጤት ደግሞ ፖለቲካውን ከኋላቀርነት ነፃ ያወጣዋል፤ ድህነትን የማሸነፍ ጥረትንም ቀላል ያደርገዋል።
ጦርነት እንደጥላ በሚከተላት ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮችን ጠንካራ ተቋማትን በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህል ተለምዷዊ ይሆናል። ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር የሚታየው ደምስሶ የመቅዳት የቆዬ ልማድም ቦታ ያጣል። ይህ ሁሉ እውን የሚሆነው ግን ጠንካራ ነፃና ገለልተኛ ተቋማት መገንባት ሲቻል ነው።
አሁን ላይ መንግሥት ብቁ አገራዊ ተቋማት እንዳልተገነቡ በማንሳት ይህ ሂደት እንዲቆም ጠንካራ ተቋማትን የመገንባት ሂደትን መጀመሩን ይፋ አድርጓል። ለዚህም በአንዳንድ ተቋማት ላይ የታየው አፍርሶ ከመገንባት ይልቅ ሪፎርምን ተከትሎ የመገንባት ስልት ብዙ ለውጦች እያሳየ ነው። ይህ ደግሞ ሀገርን ከሚያጸናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እስከ ዴሞክራሲ ተቋማት ድረስ ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማትን ለመፍጠር በመንግስት የተሰጠው ትኩረት እና ሥራውንም በትኩረት የመስራት ልምምድ ያሳየው ውጤት ኢትዮጵያን ከገባችበት ችግር ሊያወጣት እንደሚችል ተስፋ አስይዟል።
ይህ እቅድ ከግብ ከደረሰ የአገሪቱ ተቋማት ለዘመናት ከተጫናቸው ድብርት ነጻ ይወጣሉ ይህም ሲባል ብቃት ባላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ታግዘው ለሕግ የበላይነት ተገዥ ይሆናሉ እንደማለት ነው።
ተቋማት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምኅዳሩን በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ጠንካራ ተቋሞች ውጤታማ ውሳኔ ለመስጠት ማዕቀፍ የሚያዘጋጁ፣ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ እና ግልጽነትን የሚያጎለብቱ በመሆናቸው ለመልካም አስተዳደር ወሳኝ ናቸው። ነገር ግን ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ቀላል ስራ እንዳልሆነ እሙን ነው።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የሥርዓት መለዋወጥ መሠረታቸው የማይናጋ ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ሁሉም የራሱን ጡብ ማስቀመጥ ይኖርበታል።
ለዚህም ነው ብልጽግና ሁለተኛ ጉባዔውን ሲያካሂድ ካስቀመጣቸው 8 ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች ውስጥ በሁለተኛ ተራ ቁጥር እንዲህ ያለው፦ “የተቋማት ግንባታ ስኬት ለውጤታማ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በእጅጉ ወሳኝ ነው ብለን እኛ ብልፅግናዎች ከልብ እናምናለን። ከዚህ ጽኑ እምነት ተነሥተንም ዴሞክራሲን ተቋማዊና ሕዝባዊ ባህል በማድረግ የሀገረ መንግሥት ቅቡልነትን ለማረጋገጥ ወደ ተጨባጭ ሥራ ገብተናል። በመሆኑም የተጀመረውን የተቋማት ሪፎርም በየዘርፉና በየደረጃው አጠናክረን በማስቀጠልና ነጻ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸውን ተቋማት በማባዛት የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራችንን በጠንካራ መሠረት ላይ ለማቆምና ጠንካራ የዴሞክራሲ ባህል ለመፍጠር አበክረን የምንሠራ ይሆናል።”
በዚህ ነጥብ መሰረት ሀገር እያስተዳደር የሚገኘው ብልጽግና የተቋማት ግንባታ ላይ በሰፊው መስራት አስፈላጊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ጽኑ እምነቱ መሆኑ የሚያመላክት ነው። በቀጣይም የመደመር መንግሥት ዋና ትኩረቱ ሆኖ ተቋማትን በሪፎርም እየገነባ ነጻ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ይሰራል ማለት ነው። ይህ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ የዘመናት ህመም እንዲፈውስ ሊያደርግ የሚችለው አንዱ መፍትሄ።
ንብርቴ ተሆነ