Search

የከምባታ ሕዝብን የኅብረት ሥራ ባህል የሚወክለው ‘ኡቱቢያ ወገ’ አደባባይ

እሑድ ኅዳር 28, 2018 50

በከምባታ ሕዝብ ነባር ባህል መሠረት፥ አንድ ሰው ጎጆውን ሲቀልስ (ቤቱን ሲገነባ) የአካባቢው ሰዎች የማገዝ ሞራላዊ ግዴታ አለባቸው፤ ይህን ሲያደርጉ ታዲያ ቤት ገንቢው ጠይቋቸው አይደለም፤ በራስ ተነሳሽነት እንጂ።

አንድ ግለሰብ ድንገት በአባባቢው ለግሉ ጉዳይ ሲንቀሳቀስ አዲስ ቤት እየተሠራ ቢመለከት፣ የግል ጉዳዩን ለጊዜው ተወት በማድረግ እየተገነባ ላለው ቤት የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ሞራላዊ ግዴታው ነው።

የአዲሱ ቤት ግንባታ በአካባቢው ማኅበረሰብ የጋራ ርብርብ ተጠናቅቆ እየተበላ፣ እየተጠጣ ከተመረቀ በኋላ የቤቱ ባለቤት ለማኅበረሰቡ ምስጋና ያቀርባል። የቤቱ ባለቤት አዲስ ጎጆ ወጪ ከሆነ ደግሞ ለኑሮው አጋዥ የሆኑ ቁሳቁስ ከማኅበረሰቡ አባላት በስጦታ መልክ ይበረከቱለታል።

ምስሎቹ የሚያሳዩት የከምባታ ሕዝብ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚገለገልበትን ይህን የቆየ ባህላዊ ሥርዓት ለማንፀባረቅ በዱራሜ ከተማ የተበጀውን ኡቱቢያ ወገአደባባይ ነው።

ከምስሎቹ ማየት እንደሚቻለው፥ ቤት ሠሪው በጅምር ላይ ያለ ጎጆ ቤቱን ምሶሶ አቋቋም አንጋጦ እየተመለከተ ሲሆን፤ በዙሪያው ያሉት የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ሥራ ተከፋፍለው በቤት ግንባታው በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በኅብረት ከሠሩ ዓላማን በቀላሉ ማሳካት እንደሚቻል የከምባታ ሕዝብን የሥራ ባህል የሚወክለውኡቱቢያ ወገአደባባይ ያለ አስረጂ ይናገራል።

ከማኅበረሰቡ ነባር እሴት የተቀዳው የትብብር እና በጋራ የመሥራት ባህል፥ "በኅብረት፣ እንችላለን" የተሰኘውን ብሂል በተጨባጭ ተግባር የገለጠ ነው ማለት ይቻላል።

በሲሳይ ደበበ