የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ኢትዮጵያውያን ባሕላዊ ትውፊታቸውንና ልምዶቻቸውን የሚለዋወጡበት መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በዚሁ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ክልሉ በዓሉን እንዲያስተናግድ ዕድል በማግኘቱ አመስግነው፤ በዓሉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን አልፋ፣ የሕዳሴ ግድብን ባስመረቀችበት እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀከቶች በተበሰሩበት የማንሰራራት ዘመን በዓሉ በመከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በዓሉ ብሔራዊ መግባባትን በማጠናከር የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን ለማሳለጥ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አክለውም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአንድ መድረክ ተገኝተው እንዲደምቁና እንዲመክሩ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል።
ዜጎች የልዩነት ምክንያት በሆኑ ጉዳዮች መክረው እና ዘክረው የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ለማስቻል፣ የጋራ ትርክትን በፅኑ መሰረት ለማኖር እና የሐገረ መንግሥት ቅቡልነትን ከፍ ለማድረግ ለተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ክልሉ ሚናውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።
በዓሉ "ዴሞክራሲያዊ መግባባት፤ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተከበረ የሚገኘው።
በላሉ ኢታላ