ኢንዲያ ቱዴይ፣ ኤንዲቲቪ (NDTV)፣ ሒንዱ ታይምስ፣ ኒውስ ኤክስ እና በርካታ የሕንድ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ የመሳሰሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለ ሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ጉብኝት እና የሁለቱ ፓርላማዎች የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር በተመለከተ ሰፊ ዘገባ ሰርተዋል። አንዳንዶቹም የጠቅላይ ሚኒስተሩን ንግግር በቀጥታ አስተላልፈዋል።
ከዘገባዎቹ መካከልም ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለኢትዮጵያ ፓርላማ የጋራ ጉባኤ ያደረጉት ንግግር ታሪካዊ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ በሕንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጥልቅ ባህላዊ እና ታሪካዊ ትስስር አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያን "የአንበሶች ምድር" ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፣ ይህንን ከትውልድ ግዛታቸው ጉጃራት ጋር በማመሳሰል "ልክ እንደ ቤቴ ይሰማኛል" ማለታቸውን ሚሊዮኖች የሚከታተሏቸው የሕንድ መገናኛ ብዙኃን አስነብበዋል።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሳይንስ የሰው ልጆችን ጥንታዊ ዱካዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳገኘ መግለጻቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። "ዓለም ስለ 'ሉሲ' ወይም 'ድንቅነሽ' ሲናገር፣ እያወራ ያለው ስለ ቅሪተ አካላት ብቻ ሳይሆን ስለ ሁላችንም መነሻ ነው" ማለታቸውን በርካታ የሕንድ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
"ይህ መነሻ ደግሞ በአዲስ አበባም ሆነ በሕንድ ለምንኖር ለሁላችንም የጋራ ነው። በህንድ 'ቫሱዳይቫ ኩቱምባካም' (Vasudhaiva Kutumbakam) እንላለን፤ ትርጉሙም 'ዓለም አንድ ቤተሰብ ናት' ማለት ነው። ይህ አባባል ከፖለቲካ፣ ከድንበሮች እና ከልዩነቶች ባሻገር የጋራ መነሻ እንዳለን ያስታውሰናል። መነሻችን አንድ ከሆነ፣ ዕጣ ፈንታችንም የጋራ መሆን አለበት" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት ልክ እንደ ቤቴቸው እንደተሰማቸው ገልጸው፣ ለዚህ አፍሪካዊ ሀገር ፓርላማ ንግግር ማድረግ "ትልቅ ክብር የሚሰጠው አጋጣሚ" ሲሉ ገልጸውታል።
በጥንት ዘመን በአዱሊስ እና በርበራ፣ በሕንድ ውቅያኖስ ሁለቱ ሀገራት የተጠናከረ የንግድ ግንኙነት እነደነበራቸው አስታውሰው፤ አሁን ይህ የምርት ልውውጥ ወደሃሳብ ልውውጥ እና ወደተሻለ ደረጃ ማደጉን አጽንኦት መስጠታቸውንም መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።
የአዲስ አበባን፣ ባህር ዳር እና መቐለ ከተሞችን ስም እያነሱ በምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ራኔንድራ ሞዲ፤ የኢትዮጵያ እና ሕንድ ጥብቅ ትስስርን እያነሱ እና ከታሪክ ጋር እያጣቀሱ የኢትዮጵያን ልዕልና አወድሰዋል።
"በዚህ ዴሞክራሲ በተስተናገደበት አዳራሽ፣ በሀገሪቱ እምብርት፣ እንዲሁም ጥንታዊ ጥበብ እና ዘመናዊ ራዕይ በሚገናኙበት ስፍራ በመገኘቴ ክብር ይሰማኛል። ለፓርላማችሁ፣ ለሕዝባችሁ እና ለዴሞክራሲያዊ ጉዞአችሁ ያለኝን ጥልቅ አክብሮት ይዤ ወደ እናንተ መጥቻለሁ። በ1.4 ቢሊዮን የሕንድ ህዝብ ስም የወዳጅነት፣ የመልካም ምኞት እና የወንድማማችነት ሰላምታን አቀርብላችኋለሁ" ሲሉ መናገራቸውንም መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ለተሰጣቸው ታላቅ የክብር ኒሻን ሽልማት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ሽልማቱንም ለ1.4 ቢሊዮን የሕንድ ሕዝብ አበርክቻለሁ ማለታቸውም ተዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋራ እሴቶችን በማንሳት፣ ሁለቱም ሀገራት መሬታቸውን እንደ "እናት" እንደሚያከብሩ ገልጸው፤ የወደፊቱ ጊዜ በቅንጅት እና "ዓለም አንድ ቤተሰብ ናት" በሚለው ስሜት ላይ እንዲገነባ ጥሪ አቅርበዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም
#Ebcdotstream #EBC #Ethiopia #India #Diplomacy