የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ለዓመታት ተጥለው ከቆዩ በኋላ በራስ አቅም ሙሉ እድሳትና ሙከራ ያደረገላቸው፣ ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ በርካታ ሜካናይዝድ ትጥቆችን ዛሬ ለመከላከያ ሜካናይዝድ ዕዝ በማስረከብ ወደ ኃይል አስገብቷል።
በመርሐ ግብሩ በመገኘት ትጥቆቹን የጎበኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፥ የዋና መምሪያውና የጥገና ማዕከሉ አመራር፣ ባለሙያ እና አባላት ተዓምር ሊባል የሚችል ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

ሥራው ሀገርን በቢሊዮን ከሚቆጠር ወጪ ከማዳኑ ባለፈ፤ ፈጠራን በማሻሻል በራስ አቅም ተዓምራዊ ሥራ ማከናወን እንደምንችል አሳይቷል ብለዋል።
ለዓመታት አረም ወርሷቸው ከቆዩ በኋላ ወደ ኃይል የገቡት የሀገር ሀብቶች የሠራዊቱን የውጊያ ዝግጁነትና አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ትጥቆቹ ተቀብሮ የቆየ የሀገር ሀብት ጥቅም ላይ የዋለባቸው ብቻ ሳይሆኑ፤ የመከላከያ ሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ የደረሰበትን ደረጃም የሚያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተቋሙ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ውጤታማ ተግባራትን ላከናወኑ የዋና መምሪያው አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል።
የተጀመሩ የእድሳትና የፈጠራ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለሀገር እና ለተቋም ጥቅም እንዲውሉ የማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ማሳሰባቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዝግጅቱ ላይ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮች ተገኝተዋል።