ቴክኖሎጂ የተለዋዋጩ ምኅዳር ዘዋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ በቂ የሚባል የተጠቃሚነት ድርሻን አላገኙም። ለዘመናት የተላመዱት የተቀባይነት ሚና በራስ ያለመቆምን የሚያለማምድ እና ሉዓላዊነትን የሚጎዳ ነው።
በቴክኖሎጂ ውድድር ይህን ዕሳቤ ማራመድ እና ከሌሎች የተገዛ ሲስተም ተቀባይ ብቻ መሆን አዋጭ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዚህ ዕሳቤ እንደተጀመረ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጎልብቶ እና በልፅጎ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ባለፈው የዲጂታል ስትራቴጂ ንቅናቄ ወቅት ለአፍሪካም ዋቢ መሆን የሚችል የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ኢንስቲትዩት መገንባት ስለመቻሉ ገልጸው፤ ተቋሙ በሚመሠረትበት ወቅት ልምድ ለመቅሰም እንኳ የሚያስችል ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአህጉሪቱ እንዳልነበር አስታውሰዋል።
እንዲሁም ባለፉት ጊዜያት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ለማድረግ ቢታቀድም፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ትግበራ ባለመኖሩ ምክንያት ሃሳቡ ሳይተገበር መቆየቱን አስረድተዋል። አሁን ላይ ግን በቴክኖሎጂው እገዛ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሊተገበር መቻሉን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ “የመጣውን ሁሉ ስንከተል ኋላ ቀርተናል፤ ይህ ስለሰለቸን ከቻት ጂፒቲ እና ከዲፕ ሲክ ቴክኖሎጂዎች ጋር ሊገዳደር የሚችል መላ የተሰኘ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ልንፈጥር ችለናል በማለት የቴክኖሎጂ ሽግግሩን አመላክተዋል።
አያይዘውም የአፍሪካ ሀገራት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ከተቀረው ዓለም አምጥተው ብቻ ሲጠቀሙ ለዘርፈ ብዙ ጫናዎች እንደሚጋለጡ ጠቁመው፤ በአፍሪካውያን የበለፀጉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እና አሠራሮችን መተግበር ራሱን የቻለ ዋስትና እንዳለው አመላክተዋል።
በአፎምያ ክበበው