Search

ሕዝባዊ ውይይቶች የሰላም እና ፀጥታ መሠረት ናቸው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ሰኞ ታኅሣሥ 13, 2018 355

የኢትዮጵያችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ላይ የተመሠረተ ነው። ሰላም ለሰው ልጅ ዕድገትም ሆነ ለሀገር ግንባታ ሂደት ዋንኛው መነሻ ነው።
ሰሞኑን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች የሕዝብ ድምፅ ጎልቶ እንዲሰማ ማድረጋቸውን እና ሕዝቡ ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ቁርጠኛ መሆኑ የታየበት ሁነኛ መድረክ እንደነበር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች የሀገሪቱን ሰላም እና ፀጥታን፣ እንዲሁም የተያዘውን የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ ሀገራዊ አንድነቱን የሚሸረሽሩ አዝማሚያዎችን መከላከል እና መቆጣጠር ቁልፍ ሥራ መሆኑን አንሥተዋል።
በተለይም ሰላም እና ፀጥታን ማስፈን የሙሉ ጊዜ ሥራ በመሆኑ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት መከታተል፣ መጠበቅ፣ ከመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ጋር በቅርበት መሥራት አዋጭነቱ የጎላ መሆኑን ማመላከቱን ነው አገልግሎቱ የገለጸው።
መድረኮቹ የሕዝቡን ድምፅ ከማጉላት ባለፈ በዜጎች እና በመንግሥት ተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያግዝ እንደሆነም ጠቁሟል።
በየጊዜው የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በግልጽ በመፍታት እና መፍትሔዎችን በማቅረብ የመተማመን እና የትብብር ድልድይ እንዲፈጠር ስለማስቻሉም አክሏል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ለሰላም ዘብ መቆም ከሁሉም የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን በመግለጽ የእኩይ ኃይሎች ተግባራትን ለመከላከል መንግሥት ቀጣይነት ያለው እርምጃ እንዲወስድም ጥሪ አቅርበዋል።
ሰላም እና ፀጥታን ማስፈን የዜጎች ሙሉ ተስፋ፣ ነፃነት እና ክብር መረጋገጥ ላይ ሚናው የጎላ ነው ያለው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ለዚህ ደግሞ ሕዝባዊ የውይይት ሂደቶች ለሀገራዊ አንድነት እና ጽናት እያደገ የመጣውን የመንግሥትን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክቱ ጠቁሟል።